የመዲናዋ የቱሪዝም ማዕድ

You are currently viewing የመዲናዋ የቱሪዝም ማዕድ

ባህላዊ ምግቦችና የአመጋገብ ስርዓት ለዓለም የሚታይበት የምግብ ፌስቲቫልና ኤክስፖ በመዲናዋ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል

“ታህሳስ ወይ ቀብራሬ

ይህን ሁሉ ይዘህ ምነው እስከዛሬ”

ይላሉ አበውና እመው ባለመልከ ብዙውን የታህሳስን ወር በሥነ ቃል ሲገልፁት፡፡ ታህሳስ ደመናው ጠፍቶ የሌሊቱ ቁር (ብርድ)፤ የቀኑ ሐሩር የሚበረታበት፣ አርሶ አደሩ የዘራውን እህል የሚያጭድበትና እየወቃ ወደ ጎተራ የሚያስገባበት፣ ጥጋብ ያለበት ወር ነው፡፡ የጥር ወርም ሰማይ የደመና ልብሱን ጥሎ ራቁቱን የሚታይበት፣ ቀን ፀሐይ፣ ሌሊት ከዋክብትና ጨረቃ በጠራው ሰማይ የሚታዩበት፣ ወንዞች የሚጎድሉበት፣ ሠርግና ኃይማኖታዊ በዓል የሚከናወኑበት ነው፡፡ 

የታህሳስ እና ጥር ወራት ከተፈጥሮ ባሻገር ሰው ሁሉ አምሮ፣ ተውቦና አጊጦ በአደባባይ የሚታይበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ወደተለያዩ አካባቢዎች ለመንቀሳቀስና ጉብኝት ለማድረግ ምቹ ጊዜም ነው፡፡

የታህሳስና ጥር ወራት በኢትዮጵያ የቱሪስቶች ወቅቶች ናቸው፡፡ በርካታ ቱሪስቶች ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፋሉ፡፡ በእነዚህ ወራት የገና እና ጥምቀት በዓላት በታላቅ ድምቀት ይከበራሉ፡፡ የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ከተመዘገቡ፣ በአደባባይ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩና በርካታ የውጭ ቱሪስቶች ከሚታደሙባቸው በዓላት መካከል አንዱ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ የቱሪዝም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ሙለታ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፣ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ እና ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች የሚኖሩበት አካባቢ በአሁኑ ጊዜ ክረምት የሚገባበት፣ በረዷማ እና አስቸጋሪ የአየር ጸባይ የሚታይበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ቱሪስቶች ወደ ሞቃታማ ሀገር በመምጣት የእረፍት ጊዜያቸውን ማሳለፍ ይፈልጋሉ፤ ወደ ኢትዮጵያም በርካታ ቱሪስቶች ይመጣሉ።

አዲስ አበባ ከዚህ ለመጠቀም ምን እየሰራች ነው?

የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና፣ በዓለም ላይ ከኒውዮርክና ጀኔቭ በመቀጠል ሶስተኛዋ የዲፕሎማሲ ከተማ፣ ወደ አፍሪካና ኢትዮጵያ መግቢያ ዋነኛዋ በር የሆነችው አዲስ አበባ በጽዳትና ውበቷ፣ ባላት መሰረተ ልማትና በምታቀርበው አገልግሎት ከፍተኛ ለውጥ እያሳየች ትገኛለች፡፡ ይህንንም ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳትሆን ለጉብኚት፣ በተለያዩ ኮንፈረንሶች፣ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች ለመታደም የመጡ የውጭ ሀገር ዜጎችም በመደነቅ ምስክርነት የሚሰጡበት ጉዳይ ነው፡፡

በያዝነው ወርና በጥር ወር ወደ ሀገራችን የሚገቡ ቱሪስቶች በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲጎበኙና ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እየሠሩ እንደሚገኙ አስጎብኚ ድርጅቶች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን ይገልጻሉ፡፡

አቶ ናሆም አድማሱ የፕሌዠር ኢትዮጵያ አስጎብኚና የጉዞ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በቱሪዝሙ ዘርፍ በአስጎብኚነት ሰርተዋል፤ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ “በኢትዮጵያ ከመስከረም እስከ ጥር ድረስ በርካታ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበት፣ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ለማየት የሚመርጡበትና በስፋት ወደ ሀገሪቱ የሚመጡበት ወቅት ነው” ይላሉ፡፡

በዚህ ወቅት የሚመጡ ቱሪስቶችን በመቀበል መዳረሻ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ለማድረግና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ እየሰሩ እንደሚገኙ አቶ ናሆም ይናገራሉ፡፡ ቱሪስቶች በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪዝም መስህቦችን ከመጎብኘት ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እንደ ብሔራዊ ሙዚየም፣ አንድነት፣ እንጦጦና ወዳጅነት ያሉ ፓርኮችንና ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንደየፍላጎታቸው እንዲጎበኙ እንደሚያደርጉ ይገልፃሉ፡፡ “አዲስ አበባ በርካታ የቱሪዝም መስህቦች አሏት፡፡ ቱሪስቶች የጉብኚት ጊዜያቸውን ሲያሳውቁን ያሉትን መስህቦች አቅርበን፤ በፍላጎታቸው መሰረት የሚመርጡትን እንዲጎበኙ እናደርጋለን፡፡ እየከፈሉ ከሚጎበኙት ባሻገር እንደ መርካቶ ያሉ ክፍት የገበያ ቦታዎች (Open air markets) በተለይ እንደ ቅመም ተራ፣ ምናለሽ ተራ፣ መሶብ ተራ ባሉ አካባቢዎች የእደ ጥበብ ስራዎችንና መልሶ ጥቅም ላይ የሚውሉ እቃዎችን እንዲመለከቱ እናደርጋለን” ይላሉ፡፡ 

በጎዳናዎች ሲንቀሳቀሱም ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ባላቸው ሀገራት፣ ለኢትዮጵያ ውለታ በዋሉ ዜጎች ስም ስያሜ የተሰጣቸው እንደነቸርችል፣ ደጎል አደባባይ፣ ሜክሲኮና ሌሎች መንገዶችና አደባባዮች ስያሜው ለምን እንደተሰጣቸው በማስረዳት ጉብኚት እንዲያደርጉ ይደረጋል፡፡

አቶ ናሆም እንደሚገልፁት፣ ከውጭ እንግዶች በግልም ሆነ በቡድን ሆነው ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሲፈልጉ የሚፈልጉትን የቱሪዝም መዳረሻና አገልግሎት በማካተት ምን ያህል ዋጋ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ በቀረበው ዋጋ ሲስማሙ ሌሎች አገልግሎቶችን ከሚያቀርቡ አካላት ጋር በመሆን አገልግሎቱን እንዲያገኙ ይደረጋል። ከመነሻቸው ጀምሮ ወደ ሀገራቸው እስኪመለሱ ድረስም ጥሩ ነገሮች አይተው፣ ስለ ኢትዮጵያ የተሻለ ግንዛቤ ይዘውና ተደስተው እንዲሄዱ፣ ከተመለሱ በኋላ ለቤተሰቦቻቸውና ለጓደኞቻቸው ስለኢትዮጵያ ጥሩ እንዲናገሩ የሚያደርግ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል፡፡

በመዲናዋ በርካታ የቱሪዝም መስህቦችና መዳረሻዎች መኖራቸው ለቱሪስቶች ከተማዋን እንዲጎበኙና ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የሚያበረታቱ መሆናቸውን አቶ ናሆም ይገልፃሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የተከፈተው አፍንጮ በር አካባቢ የሚገኘው የ“እንስራ የሸክላ ስራ ማምረቻ፣ ማሳያና መሸጫ ማዕከል” ከውጭ የሚመጡ ቱሪስቶች ተመራጭ የሆነ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ስፍራ የሸክላ ስራ ከመነሻው እስከ መጨረሻ ምርት ሂደት ድረስ ይታይበታል፡፡ ስራው የሚከናወንበት ቤትም ታሪካዊ ቤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ እና ሌሎች መዳረሻዎች ሲጨመሩ ኢትዮጵያ በዓለም ሰላምን በማስጠበቅና ፓን አፍሪካኒዝምን በማጠናከር የተጫወተችውን ሚና አጉልቶ ለማሳየት ያስችላል፡፡

ቱሪስቶች ወደ አዲስ አበባ ሲገቡ በመጀመሪያ ቀን በከተማዋ የተመረጡ መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ከተደረገ በኋላ ቀጥሎ  መሄድ ወደሚፈልጉባቸው  የሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ይጓዛሉ። ቱሪስቶች የፈለጉትን ብቻ ሳይሆን ያለውንም በማሳወቅ እንዲጎበኙ እናበረታታለን፡፡  አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መዳረሻዎችን ጎብኝተው ቀድመው ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ሆቴል ከመቀመጥ ይልቅ ያላዩትን የቱሪዝም መዳረሻ እንዲያዩ እንደሚያደርጉ አቶ ናሆም አብራርተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ምን ዝግጅት እያደረገ ነው?

አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿና ጎብኚዎች ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፤ በመሰራት ላይም ይገኛሉ። በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት ከተገነቡት የአንድነት፣ የእንጦጦና ወዳጅነት ፓርኮች አንስቶ የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የአዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል፣ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ከተማዋን ከመሸጋገሪያነት ወደ መዳረሻነት እንድትለወጥ አድርገዋታል፡፡ ትላልቅ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች መገንባታቸው ቱሪስቶች ከተማዋን እንዲጎበኙና ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ እያደረጉ ነው፡፡ የከተማዋ ለውጥ በዓይን የሚታይና ዓለምም ጭምር የሚደመምበት እንደሆነ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡

“አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ ሆናለች።” የሚሉት አቶ ሁንዴ፣ በከተማዋ የሚደረጉ ትላልቅ ፋይዳ ያላቸው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች፣ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች ከጊዜ ወደ ጊዜም እያደገ፤ የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ376 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር እና 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ከተማዋን ጎብኝተዋል፡፡

በታህሳስ እና ጥር ወራት በርካታ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሚያነሱት አቶ ሁንዴ፣ በእነዚህ ወራቶች በርካታ ፌስቲቫሎች፣ ስብሰባዎች፣ ኃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም ልዩ ልዩ ኹነቶች ይከናወናሉ። ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ሲመጡ የሚሳተፉበት፣ የሚዝናኑበትና የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚረዱባቸው እንቅስቃሴዎች ያስፈልጋሉ፡፡ በዚህ ረገድም የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ከጎልደን ግሩፕ ሆስፒታሊቲ ጋር በመሆን የምግብ ፌስቲቫልና ኤክስፖ (ጋስትሮኖሚ) እያዘጋጀ ይገኛል፡፡

የቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ እንደሚገልፁት፣ የምግብ ፌስቲቫልና ኤክስፖው በሚሊኒየም አዳራሽ ጥር 9 እና 10 የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦችና የአመጋገብ ስርዓት ለዓለም የሚታይበት ነው፡፡ 10 ሺህ ሰዎችም ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል። ፌስቲቫሉ በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያና አዲስ አበባ ለመምጣት ሲያስቡ የምግብ ፌስቲቫልና ኤክስፖ (ጋስትሮኖሚ) ታሳቢ አድርገው እንዲመጡ ለመሳብ ያስችላል፡፡ በአንድ ቦታ የኢትዮጵያን ምግብና ባህል የሚያውቁበትን አጋጣሚ በመፍጠር ቆይታቸውን ለማራዘም፣ የአዲስ አበባንና የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን በታህሳስና ጥር ወራት ለሚመጡ ጎብኚዎች የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻዎች ከማስተዋወቅ ባሻገር የመዳረሻ ቦታዎችን የሚጎበኙበትን ሁኔታ እያመቻቸ ይገኛል፡፡ በተያዘው ታህሳስ ወር “የዲሴምበር ፓኬጅ” የተሰኘ የቱሪስት ፓኬጅ በመቅረፅ ቱሪስቶች በመዲናዋ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦችን በአነስተኛ ዋጋ በአንድ ፓኬጅ መጎብኘት የሚችሉበትን ዕድል በማመቻቸት መስህቦችን ለማስተዋወቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በአንድ ጊዜ አንድ ወይም ሁለት መዳረሻዎችን ለመጎብኘት በሚጠይቅ የመግቢያ ክፍያ አንድነትና ወዳጅነት ፓርኮችን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም፣ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ሙዚየም፣ ዓድዋ ድል መታሰቢያን እንዲጎበኙ ዕድል የሚፈጥር ነው፡፡ ይህ መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅና ጎብኚዎችን ለማበረታታት የተዘጋጀ ፓኬጅ በመሆኑ እንጂ ብሔራዊ ቤተ መንግስትን ለመጎብኘት ብቻ የሚያስከፍለው ከ500 ብር የማያንስ ነው፡፡ በዚህ ረገድም ከቱሪዝም መዳረሻ አስተዳዳሪዎች ጋር ውይይት መደረጉንና ፓኬጁ ተቀርፆ ማለቁን አቶ ሁንዴ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽኑ ራሱን ችሎ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ መስሪያ ቤት ሲሆን የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በቱሪዝሙ ዙሪያ ከሚሰሩ አስጎብኚዎችና የጉዞ ወኪሎች፣ የባለሙያዎች፣ የሆቴል ባለንብረቶች እና ሌሎች ማህበራትና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ሙለታ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ የታህሳስ እና ጥር ወራት በርካታ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የሚመጡበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህ ቱሪስቶች በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲጎብኙና ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ በማድረግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ ይገባል፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ ቱሪስት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ እንደ ብሔራዊ ሙዚየም፣ ታሪካዊ ሀውልቶች ወይም እንደመርካቶ ገበያ ያሉ ቦታዎችን ብቻ ነበር የሚጎበኘው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሰሩ አዳዲስ መናፈሻዎች፣ በኮሪደር ልማት የእግረኛ እና ሳይክል መንገዶችን በማካተት የተገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች ቱሪስቶችን ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ በእግር ሳይቀር ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉና የሚጋብዙ ናቸው። ቱሪስቶች የሚያርፉባቸው የሆቴል፣ ምግብ፣ መኝታና መሰል አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ አኳያም በስፋት እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ለቱሪስቶች ፓኬጅ የሚሸጡ አስጎብኚዎችና የጉዞ ወኪሎች በከተማዋ የተሰሩ የቱሪዝም መስህቦችን ብቻ ሳይሆን የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በማካተት መሸጥ እንደሚኖርባቸው ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ያስረዳሉ፡፡

“አሁን መንገዶች ለሶምሶማ ሩጫ (Jogging) እና እርምጃ ምቹ ሆነዋል፡፡ ጥሩ የሆነ የብስክሌት መንገድ ተሰርቷል፡፡ ከቤት ውጪ የሚደረጉ እንደ የብስክሌት ውድድር ያሉ እንቅስቃሴዎችን እንዲዘጋጁና ቱሪስቶች እንዲሳተፉ በማድረግ ቆይታቸውን ማራዘምና እርካታቸውን ማሳደግ ይቻላል፡፡ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ መስህቦችን ከጎበኙ በኋላ ተመልሰው ሆቴል ገብተው ቁጭ እንዲሉ ሳይሆን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፉበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ወደ እንጦጦ በእግራቸው እንዲሄዱ (Hiking) ማድረግም ሌላው አማራጭ ነው” ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው፡፡

በከተማዋ ጥር 9 እና 10 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው የምግብ ፌስቲቫልና ኤክስፖ (ጋስትሮኖሚ) የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም የሚያግዝ እንደሆነ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ያነሳሉ፡፡ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን ምግቦች ጣዕም የሚያውቁበትና የሚቀምሱበት በመሆኑ ትልቅ እድል ነው፡፡

የቱሪስቶችን እርካታ ለማሳደግ ጉብኝታቸውን እና የሚያሳልፉትን ጊዜ የማይረሳና ደግመው የሚናፍቁት ማድረግ ይገባል፡፡ እንዲህ ሲሆን ድጋሜ ራሳቸው መጥተው ሊጎበኙ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም መልካም የሆነ ነገር ለቤተሰባቸው፣ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው በመንገር ሌሎችም መጥተው እንዲጎበኙ ሊያነሳሱ እንደሚችሉ የቱሪዝም ጥናት ተባባሪ ፕሮፌሰር ሽፈራው ጠቁመዋል፡፡

ቱሪዝም ሲባል በየትኛውም ቦታ አገልግሎት መስጠትና መሸጥ ጋር ይያያዛል፡፡ ቱሪስቶች ነገ ተመልሰው እንዲመጡ የሚያስችሉ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ሁሉም መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ አኳያ ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው ጀምሮ ሆቴሎች፣ የንግድ ተቋማትና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ቱሪዝም የኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑን በመረዳት መዳረሻ ቦታዎችን ጨምሮ በማንኛውም ቦታ ቱሪስቶችን በአግባቡ በመቀበል፣ መረጃ በመስጠትና በማገዝ ለሀገር መልካም ገፅታ ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል እንላለን፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review