የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጤናው ሴክተር ሰራተኞች ባመቻቸው የ25/75 የቤት ልማት መርሀ ግብር ሰራተኛውን የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ቢሮው በስሩ የሚገኙ የሆስፒታል እና በሁሉም ክፍለ ከተማ እና ጤና ጣቢያ የሚሰሩ ሰራተኞችን እንዲሁም የቢሮ ሰራተኞችን በ25/75 የቤት ልማት መርሀ ግብር በማህበር ተደራጅተው የቤት ዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ከቢሮ እና በክፍለከተማ ኮሚቴ ተቋቁሞ ተኩረት እየተሰራ እንደሆነም ተመላክቷል ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ የጤናው ሴክተር ሰራተኞች ያለባቸውን የቤት ችግር ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ በ25/75 የቤት ልማት መርሀ ግብር ተደራጅተው 25 በመቶ በመቆጠብ እና 75 ፕርሰንት ደግሞ ከባንክ ጋር በሚደረግ የብድር ስምምነት የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

25 ፐርሰንት በቅድሚያ በመክፈል ለመደራጀት የተመዘገቡትን በአፋጣኝ ክፍያቸውን በማጠናቀቅ ቦታውን ተረክበው ግንባታቸውን መጀመር እንዳለባቸው ተናግረዋል ።
የተቋሙ አመራር ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሰራ ያሳሰቡት ዶክተር ዮሐንስ የተደራጁ ማህበራት በእኩል በፍጥነት እንዲሄዱ በማድረግ እና ኮሚቴውን በማገዝ ለውጤታማነቱ ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።
የቢሮው አማካሪ ወይዘሮ ብርቱካን አህመድ በበኩላቸው በ25/75 የቤት ልማት መርሀ ግብር ማህበራትን በማደራጀት ወደ ስራ እንደተገባ ገልፀው የቅድመ ክፍያው በሚገባው ፍጥነት በመጨረስ ወደ ተግባር ለመግባት መስራት ይገባል ብለዋል።
እካሁን በሁሉም ክፍለ ከተማ የሚገኙ የጤናው ዘርፍ ሰራተኞች በ27 ማህበራት በ25/75 የቤት ልማት መርሀ ግብር ተደራጅተው ክፍያ በመፈፀም ላይ እንደሚገኙ ቢሮው ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ተመላክቷል።