የኢትዮጵያ ምርቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በጥራትም ሆነ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተቋማት የእሴት ሰንሰለት መዘርጋትና በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል

You are currently viewing የኢትዮጵያ ምርቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በጥራትም ሆነ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተቋማት የእሴት ሰንሰለት መዘርጋትና በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል

AMN ታኅሣሥ 12/2018

የኢትዮጵያ ምርቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በጥራትም ሆነ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ተቋማት የእሴት ሰንሰለት መዘርጋትና በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እና የግራንድ አፍሪካ የአመራርና የተቋማት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ገለጹ።

20ኛው ግራንድ አፍሪካ የአመራርና የተቋማት ሽልማት መርሐ-ግብር ”ትጉኃንን እንሸልማለን” በሚል ቃል በአደዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተካሄዷል።

በመርሐ- ግብሩ በተለያዩ ዘርፎች ተመዝነዉ ላሸነፉ ተቋማትና የተቋማት መሪዎች እዉቅና ተሰጥቷል።

አሸናፊ ለሆኑ ድርጅቶችና የተቋማት መሪዎች እዉቅና የሠጡት የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እና የግራንድ አፍሪካ የአመራርና የተቋማት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ተሸላሚዎችን: ተወዳዳሪዎችንና የመርሃ ግብሩን አዘጋጆች አመስግነዋል።

የእዉቅናና ሽልማት መርሃ ግብሩ መካሄዱ የአምራቾችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የምርትና አገልግሎት የጥራት ደረጃና የዉድድር መንፈስ ከማሳደጉም በላይ ለተጠቃሚዉ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

ዉድድር ሲኖር ጥራት ያለዉ ምርትና አገልግሎት ለተጠቃሚዉ ማቅረብ ያስችላል ያሉት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በምርትና አገልግሎት ጥራት መወዳደር ባህል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

መወዳደር ማለት መጠላለፍ ሳይሆን ተደጋግፎና ልምድ ተጋርቶ የተሻለ ዉጤት ማምጣት መሆኑን የተናገሩት
የቀድሞ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት እና የግራንድ አፍሪካ የአመራርና የተቋማት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በተቋማት መካከል ዉድድር መኖሩ የኢትዮጵያ ምርቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በጥራትም ሆነ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛል።

ተሸላሚዎችም ሆኑ ያልተሸለሙት ተቋማት የምዘና ባለሙያዎች የሰጡትን ግብረ መልስ ስራ ላይ ማዋል እንዲሁም የሰዉ ሃይልን በማዘመንና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተወዳዳሪነታቸዉን ሊያጠናክሩ ይገባል ብለዋል።

የእሴት ሰንሰለት በአለም አቀፍ ደረጃ በበርካታ የቢዝነስ ተቋማት የሚተገበር አሠራር በመሆኑ በኮንስትራክሽን: በግብርና: በአምራችና በሌሎች ዘርፎች የተሠማሩ ተቋማት የእሴት ሰንሰለት መዘርጋትን ሊለምዱና ሊጠናክሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተቋማት መካከል የእሴት ሰንሰለት ማጠናከርና በትብብር መስራት ተወዳዳሪና አትራፊ ለመሆን ያግዛል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review