ልዩ ተሰጥዖ ወሳኝ መሰረተ ልማት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing ልዩ ተሰጥዖ ወሳኝ መሰረተ ልማት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ

AMN ታኅሣሥ 13/2018

ልዩ ተሰጥዖ ወሳኝ መሰረተ ልማት በመሆኑ ከሌሎች ልማቶች እኩል ኢንቨስት ማድረግ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠቃለያ እና በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ በይፋ የማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ ከተሳታፊዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራርያ፤ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ተወዳዳሪዎቻቸውን የሚበልጡበት አንዱ አቅም ተሽሎ መገኘት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የሚሰሩ ፈጠራዎችን እንደሚያበራታታ እንዲሁም አግዞ እንደሚጠቀምም አረጋግጠዋል፡፡

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዋነኛ ዓላማ ቢያንስ ሀገር በቀል ሮቦት፤ ስልክ እና አይፓድ መፍጠር የሚያስችል የሀርድዌር ማምረቻ የመገንባት አቅም መፍጠር መሆኑን ገልጸው ይህም ከሶፍትዌር ወጥተን ሀርድዌር የመገንባት እድል ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የቡና ኤክስፖርት በ3 እጥፍ ማደጉን በመግለጽ ይህንን በዲጂታል ማገዝና እሴት ጨምሮ መላክ እንደሚገባ እና ለዚህም መንግስት አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

መንግስት ከኢትዮጵያ ገበያ አልፈው ወደ አፍሪካ ገበያ ምርቶቻቸውን የሚወስዱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን በሙሉ አቅሙ እንደሚደግፍም ተናግረዋል፡፡

መንግስት እንደ ኤሌክትሪክ፤ መንገድና ቴሌኮሙኒኬሽን ሁሉ ልዩ ተሰጥዖ ወሳኝ መሰረተ ልማት ነው ብሎ ያምናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን አብራርተዋል፡፡

በኢንሳ የተጀመረውና ተጠናክሮ የቀጠለው የሰመር ካምፕ፣ በአብርሆት ቤተመጽሀፍት በየዓመቱ የሚሰናዳው የሮቦት ውድድር እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቅርቡ ያስጀመረው የስታርታፕ መሰረተ ልማት የተሟላለት ህንጻ ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ጥራት ያላቸው የመንግስት መስርያ ቤቶች እና ለስታርታፕ ተብለው የተዘጋጁ ቦታዎች መፈጠራቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከምንሰራው ስራ እኩል ልዩ ተሰጥዖ ላይ ኢንቨስት ልናደርግ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትናንሽ ስታርታፖች እንዲያድጉና እንዳይጠፉ ማድረግ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ድርብ ኃላፊነት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review