የአዲስ አበባ ከተማን ጽዳትና ውበት የማረጋገጥ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል

You are currently viewing የአዲስ አበባ ከተማን ጽዳትና ውበት የማረጋገጥ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል

AMN- ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ከተማን ጽዱ፣ ለኑሮ ምቹ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ “አዲስን እንደ አዲስ” በሚል መርህ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ገለጹ

ዋና ሥራ አስኪያጁ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር በመንግሥትና በሕዝብ ትብብር የተከናወኑ ተግባራት የነዋሪውን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በመርካቶና በተለያዩ ወረዳዎች የተከናወኑ የብሎክ ስታንዳርዳይዜሽን ወይም የጥሩ መንደር ግንባታ ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም በመርካቶና በተመረጡ አካባቢዎች ደረጃቸውን የጠበቁና ንጹሕ የሆኑ ሞዴል ብሎኮች መፈጠራቸውን ዋና ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

ይህ ተግባር የከተማዋን ውበት ከመጠበቅ ባለፈ ለነዋሪዎች ጤናማና ምቹ የመኖሪያና የሥራ አካባቢን መፍጠሩ የተገለጸ ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የታየው ውጤታማ ሥራ በሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ እንደገለጹት፤ እነዚህ ስኬቶች የተመዘገቡት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በቅርበት በመቀናጀት ነው። በተለይም መርካቶን የመሰሉ የንግድ ማዕከላት ጽዱና ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ መደረጉ ለከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ገዛኸኝ ዴሲሳ በበኩላቸው፤ ከተማዋን ከቆሻሻ ነፃ የማድረግ ተግባር አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ የከተማዋን ተወዳዳሪነትና ተመራጭነት የሚጨምር መሆኑን አብራርተዋል።

ነዋሪዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ አካባቢያቸውን ጽዱና ሞዴል ለማድረግ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በርካታ ትሩፋቶችን ይዘው መምጣታቸውንና ለኑሮአቸውም ትልቅ መሻሻል መሆኑን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተጀመሩ የጽዳትና የውበት ሥራዎችን በሁሉም አካባቢዎች በማስፋፋት፣ አዲስ አበባ ከተማን ለነዋሪዎቿ የምትመችና ለጎብኚዎች ተመራጭ የሆነች ዓለም አቀፍ ከተማ የማድረግ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ አስታውቀዋል።

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review