በንጹህ እጅና በንጹህ ልቦና በመስራት ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በንጹህ እጅና በንጹህ ልቦና በመስራት ብልጽግናን ማረጋገጥ ይቻላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሚያዝያ 8/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግስታቸውን ራዕይ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፣ኢትዮጵያ በአፍሪካ አውራ ሀገር እንድትሆን የሚያስችል የሪፎርም እና የልማት መሰረት እየተጣለ መሆኑን ገልጸዋል።

ብልጽግና በምኞት ሳይሆን በእውቀት፣ በትጋት እና በስራ እንደሚመጣ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እና የቴክኖሎጂ ማዕከል እንድትሆን መንግስት በጽኑ እያመነና እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህም ስኬት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በማጠናከር የኢንኩቤሽን ማዕከላት፣ፓርኮችን እና በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የሚመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማስፋፋት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ውጤታማ እንዲሆን መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለይም በማዕድን ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።

ቀደም ሲል እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ይገኝበት የነበረው የማዕድን ዘርፍ በአሁኑ ወቅት 4 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ማስመዝገብ መጀመሩ ትልቅ ለውጥ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም ማዕድን በሀገሪቱ የኤክስፖርት ዘርፍ ቀዳሚው እንዲሆን ያስቻለ ሲሆን፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችም በታሪክ ዝቅተኛ የነበረውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ የጂዲፒ ድርሻ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚለውጡት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ ረገድም ሀገሪቱን ለማዘመን ሰፊ የኦቶሜሽን ስራዎች በሁሉም አገልግሎቶች ላይ መጀመራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስረድተዋል።

የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማፋጠን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም የኤአይ ዩኒቨርሲቲ፣ የአይ ሲቲ እና ፓርኮች ግንባታ እንዲሁም አምስት ሚሊዮን ኮደሮችን የማፍራት ፕሮጀክት ወጣቱን ለዘመኑ ስራ ዝግጁ ለማድረግ ያለሙ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በፋይናንስ አቅርቦት በኩል የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታትም በካፒታል ምክንያት የሚቆሙ ስራዎችን የመለየትና የመፍታት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣መንግስት የኢነርጂ፣ የመሬት እና የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳለጥ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ውስጥ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ግልጽ ምላሽ ለማየት እየተጋ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሌብነትና አለመትጋት ሀገርን እንደማያሳድጉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣በንጹህ እጅና በንጹህ ልቦና በመስራት ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

አሁን እየታየ ያለው የሩጫ ፍጥነትና ውጤት ኢትዮጵያን ለማቅናትና ለማንሳት የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን በመሆኑ ሀገሪቱ ወደፊት ከመጓዝ እንደማትቆም በጽኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በአስር ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ አውራ ሀገር እንድትሆን ዜጎች በሙሉ ልብ ቆርጠው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በሚካኤል ኅሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review