ለጋራ ትርክት መሰረት የሚጥሉ አሻራዎች

You are currently viewing ለጋራ ትርክት መሰረት የሚጥሉ አሻራዎች

• በአዲስ አበባ ኮሪደርን ጨምሮ በተለያየ ልማት ላይ እየተካተቱ ያሉ ጥበባዊ ስራዎች ለአሰባሳቢ ትርክት አጋዥ መሆናቸው ተገልጿል

አቶ ደጀኔ ቶላ የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ነዋሪ ናቸው፡፡ ለዓይን ማራኪ ሆኖ በተገነባው “የአራዳ ፓርክ” የተሰራውን ልማት በአግራሞት እየተመለከቱ ነበር ያገኘናቸው፡፡ “በአዲስ አበባ በጥቂት ዓመት እንዲህ ዓይነት ስራ መሰራቱ ተአምራዊና አስደማሚ ነው፤ የተሰሩት ነገሮች ታይተው የሚጠገቡ አይደሉም። የወንዝ ዳርቻው ከመዝናኛነት ባሻገር ለከተማዋ ገቢ ያስገኛል፡፡ ታሪካዊ ምልክቶችና ሀብቶችን፣ የተለያዩ ዕፅዋቶች፣ ልጆችንና አረጋዊያንን ታሳቢ ያደረጉ መዝናኛዎችን አካትቶ የተሰራ በመሆኑ ለህብረተሰቡና ለከተማዋ ትልቅ ስጦታ ተደርጎ የሚወሰድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በወንዝ ዳርቻው ታሪክን የሚያስታውሱ ሐውልቶች ለምሳሌ የዓድዋ ዘማቾችን የሚያሳየው ለትውልዱ ልዩ ትርጉም ያለው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደጀኔ፣ “ታሪካችንን በልዩ መልክ እንዲታይ፣ እንዲዳሰስና ለትውልድ መማሪያ እንዲሆን የሰሩ እጆች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በዓድዋ ጦርነት አባቶቻችንና እናቶቻችን በባዶ እግራቸው ረጅም ርቀት በመጓዝ፣ ባህላዊ የጦር መሳሪያ ይዘው፣ በአጋሰስ ስንቅና ትጥቅ ጭነው ላብና ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደክመው ሀገርን አስረክበዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ልማቱን በማፋጠን የእነሱን አሻራና ታሪክ እየመዘገቡ ማስቀመጥ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡” ብለዋል፡፡

በዓድዋ የተለያየ ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህል፣ አመለካከት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ለአንድ ዓላማ ተሰልፈው የሀገርን ዳር ድንበር አስከብረዋል፡፡ ለእነሱ በየቦታው በተለያየ መልኩ መታሰቢያ መስራት ተገቢ ነው፡፡ ትውልዱ አኩሪ ታሪኮችን አውቆ ተኮትኩቶ እንዲያድግ አላደረግንም፡፡ ከዚህ አኳያ በሚስብ መልኩ በቅርፃቅርፅና ስዕል የተሰራው ማስታወሻ ትውልዱ አያቶቹ እና ቅድመ አያቶቹ ሀገርን ለማስከበር የከፈሉትን መስዋዕትነት እንዲረዳ ያግዛል፡፡ አንድነትን እና ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር አስተዋጽኦ አለው ሲሉ አቶ ደጀኔ ተናግረዋል፡፡

“ሾላ” እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ፀሐይ በበኩላቸው፣ በከተማዋ የተሰሩ የልማት ስራዎች ከፍተኛ በጀትና ጉልበት የፈሰሰባቸው ናቸው፡፡ የአዲስ አበባና ኢትዮጵያን ማንነት እንዲይዙ ተደርገው መሰራታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ፦ የአንድነትና ትብብር መገለጫ የሆነው የዓድዋ ድልን የሚዘክሩ ነገሮች በሚስብና በሚያምር መልኩ ተቀርፀው መቀመጣቸው ኢትዮጵያውያን አንድነትን፣ ሰላምንና ህብረትን እንዲያጠናክሩ ያደርጋል፡፡ ትውልዱ በትምህርት ቤትና በማንበብ ስለ ሀገሩ ከሚያገኘው በተጨማሪ የተለያዩ የማንነት መገለጫ የሆኑ ቅርሶችን በአካል በማየትና በመዳሰስ ፍቅርና አንድነትን ይማራል፡፡ አንዱ የሌላውን ባህል፣ ቅርስ፣ ባህልና ሀብት ማወቅና የአንዱ መገለጫ የሁሉም መሆኑን እንዲረዳ፣ ብሎም ‘የእኔ ብቻ ሀሳብ ትክክል ነው’ የሚለውን አመለካከት በመቅረፍ ለጋራ ትርክት ግንባታ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በገበታ ለሸገር የተሰሩ የአንድነትና የእንጦጦ ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይ እንዲሁም በዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ እና ሌሎች ልማቶች የኢትዮጵያን መልክና ማንነት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ እሴት የሚያሳዩ መገለጫዎች በቅርፃቅርፅ፣ በስዕል፣ በጽሑፍና በተለያየ ስነ ጥበባዊ ቅርፅ ሳቢ በሆነ መልኩ ተካትተው ተሰርተዋል፡፡

ለምሳሌ፦ ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ እየተሰራ ባለው የወንዝ ዳርቻ፣ አራዳ ፓርክ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ወረድ ብሎ የዓድዋ ዘማቾች የተሰባሰቡበት ቦታ የሀገርን ዳር ድንበርና ነፃነት ለማስከበር ኢትዮጵያዊያን ስንቅና የጦር መሳሪያ በፈረስ ላይ ሆነውና ጭነው፣ ጀግኖች አርበኞች ጋሻና ጦር ይዘው ወደ ዓድዋ ጉዞ ሲያደርጉ የሚያሳዩ ሐውልቶች ቆመውና በግድግዳ ላይ ስዕሎች ተስለው ይታያሉ። ነጭ ቀለም ያላቸው ፈረሶች እንዲሁም ተራራማ በሆነው መልክዓ ምድር የሚኖሩ ብርቅዬ ጭላዳ ዝንጀሮዎች በልዩ ስነ ጥበባዊ መልኩ ተሰርተው ይታያሉ፡፡

ከአራዳ ፓርክ ሳንርቅ፣ በዓድዋ ጦርነት ከተሳተፉ የጦር መሪዎች አንዱ በሆኑት ጀግናው ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ ስም ተሰይሞ ለትውልድ የተሻገረው የራስ መኮንን የመስታወት ድልድይም፣ ጀግኖች አርበኞች ይጠቀሙባቸው የነበሩ እንደ ጋሻና ጦር ያሉምልክቶችን አካትቶና የሚያምር ስነ ጥበባዊ ውበት ይዞ ተሰርቷል፡፡ የራስ መኮንን ድልድይን ተሻግረን ከጋምቤላ ሆቴል ጎን ወደ ስድስት ኪሎ በሚወስደው መወጣጫ ደረጃ አካባቢ የኢትዮጵያ መለያና ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የሆነው ቡና ብቻ የሚሸጥበትና የሚቀመስበት የቡና ፓርክ ይገኛል፡፡ በዚያው አካባቢም ባለቅኔው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ እየፃፈና እያሰላሰለ የሚያሳይ ሐውልትም ይገኛል፡፡

ወደ አንድነት ፓርክ ስናቀናም፤ በፓርኩ ውስጥ የኢትዮጵያን ካርታ ከሚያሳየው ቅርፃቅርፅ ጀምሮ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እልፍኝ በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ ህዝቦች ባህል፣ ታሪክና ወግ፣ የቱሪዝም መስህቦች የሚያሳዩ መገለጫዎች እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ በእንጦጦ ፓርክና ወዳጅነት አደባባይ፣ በኮሪደር ልማት በተለያዩ ስፍራዎች ጥቅም ላይ የዋሉ ቁሳቁሶች፣ ቅርሶችና የተለያዩ ምልክቶች ባህላዊና ሀገራዊ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ “የኢትዮጵያ ማንሰራራት ማሳያ፦ የወንዝ ዳርቻ” በሚል ርዕስ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአራት ወራት በፊት በተላለፈው ጥናታዊ ፊልም ላይ እንደተናገሩት በአራዳ ፓርክ የዓድዋ ዘማቾችን ታሪክ የሚያሳዩ ሐውልቶች እንዲቆሙ የተደረገው ለቱሪስት መስህብነትና ትውልድ እንዲማርባቸው ለማድረግ ታስቦ ነው። “ታሪካችንን ማቅለል አይገባንም፡፡ ለትውልድ ለጋራ ትርክት መገንቢያችን ነው፡፡ ዓድዋ ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆን፣ ሀይል፣ አቅምና ሀሳባቸውን በማሰባሰብ ሀገራቸውን የታደጉበት፣ ዛሬ የምንኮራባትን ሀገር ያስረከቡን አበውና እመው በምን ሚስጢር ነው? የሚለውን ትውልዱ የሚማርበትን ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል፡፡

በጂማ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ኑሩ ይማም ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ሲራመድ የነበረው ትርክት ለልዩነት ከፍ ያለ ቦታ የሰጠ፣ አንድነትን ደግሞ የዘነጋ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያንን ከማሰባሰብ ይልቅ ሁሉም በየአካባቢው፣ በየጎራው የራሱን ትርክት ፈጥሮ እንዲንቀሳቀስ በር የከፈተ ነበር፡፡ የተለያዩ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን የሚወክሉ ሐውልቶችና ምልክቶች፣ የተለያዩ የስነ ጥበብ ስራዎችም ከአሰባሳቢነት ይልቅ ለተናጠል ትርክት እንዲውሉ ይሰራ ነበር።

አዲስ አበባ አዳዲስ በተገነቡና በታደሱ ሙዚየሞች፣ በኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ በፓርኮች የኢትዮጵያውያን ማንነት መገለጫዎችን፣ ታሪኮችንና ጀግኖችን በተለያየ ስነ ጥበባዊ መልኩ መሰራቱ አሰባሳቢ ትርክት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል፡፡ አዲስ አበባ ውብና ፅዱ እንድትሆን ማድረግ ብቻ ሳይሆን በልዩነት ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር ከፍተኛ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ጥረት የሚበረታታ ነው ይላሉ የታሪክ ምሁሩ ኑሩ፡፡

ሌላው እንዲህ ዓይነቱ ስራ የአዲስ አበባን ብሔራዊ ምልክትነት ያሳድጋል። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን የሚያዩበት ሁኔታ ይፈጥራል። ለምሳሌ፦ አንድ ከውጭ ሀገር የመጣ ቱሪስት አዲስ አበባን ሲጎበኝ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙ ቅርሶችን፣ ምልክቶችን፣ ታሪካዊ ሁነቶችን በቀላሉና በአጭር ጊዜ መረዳት ይችላል፡፡ ኢትዮጵያውያንም በአንድ ቦታ ብዙ ታሪኮችን መረዳት እንዲችሉ በማድረግ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ እንዲከባበሩና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ በር ይከፍታል። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የመካተት ምልክታዊ ስሜትም ይፈጥራል፡፡ ከከፋፋይ ትርክት ወደ የጋራ ትርክት ለሚደረገው ጉዞ መሰረት በመሆን እንደሚያገለግል የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያውያን የጋራ የድልና ከፍታ ምልክት ከሆኑ ታሪኮች መካከል የዓድዋ ድል ዋነኛው እንደሆነ የሚያነሱት የታሪክ መምህሩ፤ ይህንን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚኮራበት፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሆ ብሎ ዘምቶ የተሳተፈበት የጋራ ድል ማጉላት ለብሔራዊ ትርክት ግንባታ ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል፡፡

አቶ አገኘሁ አዳነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአለ ሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ዲን ናቸው፡፡ ቅርፃቅርፅ፣ ስዕል፣ ስነ ጽሑፍ፣ ሙዚቃና ሌሎች ሥነ-ጥበባዊ ስራዎች ብሔራዊ መስተጋብር፣ የወል እሴት በመገንባት፣ የጋራ እምቅ የሆኑ ሀብቶችን የመዘከርና ለትውልድ የማስተላለፍ ተፈጥሯዊ ጠባይና ጉልበት አላቸው፡፡ የአደጉ ሀገራትም ሥነ-ጥበብ ላይ በመስራታቸው ከተሞቻቸው የተዋቡ ናቸው፡፡ በሥነ-ጥበብ አማካኝነት የሚተላለፉ እሴቶች ማህበረሰቦቻቸው የሰለጠኑና የለሙ ናቸው ይላሉ፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ መልሶ በመገንባት ለነዋሪዎችና ጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን መገንባት ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊጠቀሜታ ባሻገር ማህበረሰባዊ ሁለንተናዊ ልማት በማምጣት፣ የሰለጠነ ሥነ-ጥበብን ማጣጣም የሚችል ባህል ያለው ማህበረሰብን ለመገንባት ከፍተኛ ጥቅም ይኖረዋል፡፡ በዚህ ረገድ በመዲናዋ በተገነቡና እየተገነቡ ባሉ ልማቶች ጥበባዊ በሆነ መንገድ የጋራ ትርክትን መገንባት የሚያስችሉ ታሪኮችንና ሀብቶችን ማስቀመጥ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለው የበለጠ አጠናክሮ መስራት እንደሚገባም አቶ አገኘሁ ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ብዙዎቹ የአደባባይ ሐውልቶችና መሰል የሥነ-ጥበብ ስራዎች በውጭ ሀገር ሰዎች የተሰሩ እንደሆኑ ያነሱት አቶ አገኘሁ፤ በጊዜ ሂደት ብቁ ሙያተኞችን በማፍራት ሀገሪቱ በራሷ ሙያተኞች መስራት መቻል ትልቅ እምርታ ነው፡፡ ብዙዎቹ በከተማዋ በተሰሩ ልማቶች ላይ የተቀመጡ ሥነ-ጥበባዊ ስራዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ተመርቀው የወጡ ባለሙያዎች አሻራ ናቸው፡፡

ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ ባለው የወንዝ ዳርቻ ልማት የሚካተቱ የሥነ-ጥበብ ስራዎችን በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የሥነ-ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት በማማከር እየተሳተፈ ይገኛል፡፡ ስራዎቹን በመስራት የሚሳተፉትም ከትምህርት ቤቱ የተመረቁ እንደሆነ አቶ አገኘሁ ጠቁመዋል፡፡

“ሥነ-ጥበባዊ ስራዎች የሚያስተምሩ ሳይመስሉ ነው የሚያስተምሩት፡፡ የአስገዳጅነት ጠባይ የላቸውም፡፡ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት የጥበብ ስራዎች ትህትና እና ኮስታራነት ተባብረው የሰው ልጅ እንደሚማር ሳያውቅ የሚያስተምሩ ዘርፎች ናቸው፡፡” የሚሉት አቶ አገኘሁ፣ ሥነ-ጥበባዊ ስራዎች ከተዝናኖት ባሻገር ማህበረሰባዊ የወል ትርክት ለመፍጠር ያገለግላሉ፡፡ የሰለጠነ ባህል ያለውና ሥነ-ጥበብ ማጣጣም የሚችል ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል፡፡ ልጆች የጥበብ ስራዎችን እያዩ ሲያድጉ ነገ አካባቢያቸውን መረዳት፣ መጠበቅና መተርጎም የሚችሉ ሆነው እንዲያድጉ ማድረግ ያስችላሉ ሲሉ ፋይዳቸውን አብራርተዋል፡፡

የታሪክ መምህሩ ኑሩ ይማም እንደሚናገሩት፣ ኢትዮጵያን የማዘመን ጥረት የኢትዮጵያን ማንነትና ምልክቶችን ባካተተ መንገድ መሆን አለበት፡፡ ከውጭ ቀድቶ ሙሉ በሙሉ የሌሎች ሀሳብና ምልክቶችን አምጥቶ ማስቀመጥ ከአሁን በፊት የነበረው የዘመናዊነት አረዳድ ነው፡፡ አሁን ላይ ግን በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የሚሰሩ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎሉና ለጋራ ትርክት ግንባታ የሚሆኑ ሥነ-ጥበባዊ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡

ሀገራዊ ትርክትን ለመገንባት የሚሰሩ ስራዎችን አካታች በማድረግ የመገለል ስሜትን በማስወገድና የጋራ መንግስታዊ ባለቤትነትን በማጠናከር መስራት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ብዝሃነት ያለባት ሀገር ናት፤ ብዝሃነቷ በአንድነት ውስጥ የሚታይ መሆኑን የሚያሳዩ ልማቶችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አክለው አስገንዝበዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review