ከግድቡ ወደ ወደቡ፣ ከስም ወደ ተስፋ የብልፅግና አሸናፊ ልዩ የልደት ድግስ በሆሳዕና!

You are currently viewing ከግድቡ ወደ ወደቡ፣ ከስም ወደ ተስፋ የብልፅግና አሸናፊ ልዩ የልደት ድግስ በሆሳዕና!

AMN – ታኅሣሥ 18 ቀን 2018 ዓ.ም

የልጆቻቸውን ስም ከወቅታዊ የሀገር ግብ ጋር በማገናኘት በማውጣት የሚታወቁት የሆሳዕናው መምህር አሸናፊ፣ ሁለተኛ ልጃቸውን ብልፅግና አሸናፊን 4ኛ ዓመት የልደት ሻማ አብርተውለታል።

ይህ በዓል ተራ የልደት ድግስ ሳይሆን፣ የሀገር ፍቅር ስሜት እና የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምኞቶች የተሰባሰቡበት ታላቅ ክስተት ነበር።

ከክስተቶቹ አንዱ የሆነው ለብልፅግና አሸናፊ ልደት በተዘጋጀ ነጭ ቲቨርት ላይ ያረፈው መልእክት ነው።

“የሚያምርብን ስንደመር ነው!” ይላል በልብሱ ላይ የታተመ መልዕክት፡፡

በዕለቱ የታደሙ እንግዶች ዓይን ያረፈው በባለ ልደቱ ኬክ ላይ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡ በለበሱት ቲሸርት ላይ ነበር።

መምህር አሸናፊ የለበሱት ቲሸርት “የሚያምርብን ስንደመር ነው” የሚል ጥልቅ ሀገራዊ ፍልስፍናን አንግቧል።

የእናቱ ቲሸርት “ከግድቡ ወደ ወደቡ” የሚል ወቅታዊ እና የልማት ቀጣይነትን የሚገልጽ መሪ ሀሳብ ይዟል።

መምህር አሸናፊ ለዚህ ተግባራቸው ሲናገሩ “የልጆቼ ስም የኢትዮጵያውያን ተስፋ ነው። ሕዳሴን አሳክተናል፤ ቀጣዩ ህልማችን ደግሞ በሴራ ያጣነውን የወደብ ባለቤትነት ማረጋገጥ ነው” በማለት የልጆቻቸውን ስም ከሀገር ግብ ጋር አስተሳስረውታል።

“እኔ የኮሎኔል በዛብህ ልጅ ነኝ!”

የእለቱ ኮከብ የነበረው ህጻን ብልፅግና አሸናፊ፤ በኮልታፋ አንደበቱ በሆሳዕና ከተማ መሃል ሀውልት ለቆመላቸው ጀግና ክብር በመስጠት “እኔ የኮሎኔል በዛብህ ልጅ ነኝ፤ ስሜም ብልፅግና አሸናፊ ይባላል” በማለት የታዳሚውን ልብ ሰርቋል። ይህ የሕጻኑ ንግግር ስያሜው ከጀግንነት ታሪክ ጋር መቆራኘቱን ያሳየበት አጋጣሚ ነበር።

ቀጣዩ ስም ማን ይሆን? !

የብዙዎች ጥያቄ የነበረው “ቀጣዩ ልጅ ማን ሊባል ነው?” የሚለው እንቆቅልሽም ምላሽ አግኝቷል። መምህር አሸናፊ እንደገለጹት፤ ለአራተኛ ልጃቸው ያዘጋጁት ስም “ወደብ” የሚል ይሆናል።

ይህም ኢትዮጵያ በባሕር በር ባለቤትነት የምታደርገውን ጥረት በታሪክ መዝገብ ላይ በልጃቸው ስም ለማስፈር ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ ነው።

“ብልፅግና” በስሙ እንደተሰየመለት ሁሉ፣ ዕድገቱ በጤና፣ በጥበብ እና በብልጽግና የታጀበ ይሁን!

ውድ አንባቢዎች፦

የመምህር አሸናፊን የስያሜ ፈጠራ እና የሀገር ፍቅር እንዴት ታዩታላችሁ? “ወደብ” የሚለው ቀጣይ ስምስ ምን ተሰማችሁ? ሐሳባችሁን በኮሜንት አጋሩን!

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review