ሕጋዊ ያልሆኑ የውጭ ማስታወቂያዎችን ተጠቅመው በተገኙ አካላት ላይ የዕርምት ርምጃ ተወሰደ

You are currently viewing ሕጋዊ ያልሆኑ የውጭ ማስታወቂያዎችን ተጠቅመው በተገኙ አካላት ላይ የዕርምት ርምጃ ተወሰደ

AMN – ታኅሣሥ 18/2018 ዓ.ም

በአንድ ወር ጊዜ ከ5,560 በላይ ሕጋዊ ያልሆኑ የውጭ ማስታወቂያዎችን ተጠቅመው በተገኙ አካላት ላይ የዕርምት ርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በባለሥልጣን መ/ቤቱ የውጭ ማስታወቂያ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማቸው ጌታነህ፤ የከተማውን ደረጃ በማይመጥን መልኩ ማስታወቂያዎች እንዳይሰቀሉና እንዳይለጠፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ የሚሰቀሉ ማስታወቂያዎች የከተማዋን ደረጃ በሚመጥን መልኩ ዲጂታል ማስታወቂያዎችን እንዲሰቀሉ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ቀደም ሲል ሕገ ከተማዋን የማይመጥኑና ያልተፈቀዱ ዓይነት ማስታወቂያዎችን በማንሳት ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው እንዲሠሩና ወደ መስመር እንዲገቡ ጥረት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ቀደም ሲለ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ቢሠራም በርካቶች ወደ ሕጋዊ መስመር ባለመግባታቸው በሕገወጥ ድርጊት ፈፃሚዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ እና በገንዘብ እንዲቀጡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በዚህም መሰረት በአንድ ወር ብቻ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች ሕጋዊ ያልሆኑ ማስታወቂያዎች የሰቀሉትንና የለጠፉን 5,560 አካላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ ሕጋዊ እርምጃ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ዳይሬክተሩ አሁንም ፈቃድ የሌላቸው ፈቃድ እንዲወስዱና ወደ ሕጋዊ መስመር እንዲገቡ፤ ማሳደስ ያለባቸውም በወቅቱ እንዲያሳድሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በአንዋር አህመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review