ከቤት መባረር ወደ ተስፋ መፈንጠቅ የሰዎቹን ሕይወት ያሻገረው የሌማት ትሩፋት

You are currently viewing ከቤት መባረር ወደ ተስፋ መፈንጠቅ የሰዎቹን ሕይወት ያሻገረው የሌማት ትሩፋት

AMN – ታኅሣሥ 19/2018 ዓ.ም.

ለአቶ ጌጡ አባተ ሕይወት የዳገት ጉዞ ነበረች። በአካል ጉዳት ምክንያት እንደልብ መሯሯጥ ባይችሉም፣ በሊስትሮ ሥራ የሚያገኙዋትን ጥቂት ሳንቲሞች እየቆጠቡ ኑሮን ለማሸነፍ ይታገላሉ። ሆኖም የኑሮ ውድነቱና የቤት ኪራይ ጫናው ከአቅማቸው በላይ ሆኖ፣ ባለቤታቸውንና ልጃቸውን ይዘው ከሚኖሩበት ቤት ተባርረው ለከፋ እንግልት ተዳርገው ነበር።

“የቤት ኪራይ መክፈያ አጥቼ ከቤት ተባርሬ ነበር” የሚሉት አቶ ጌጡ፣ ያ የጨለማ ጊዜ አልፎ ዛሬ በፊታቸው ላይ አዲስ ተስፋ ይነበባል። ይህ ተስፋ የመነጨው ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ እየተተገበረ ባለው የ”ሌማት ትሩፋት” ንቅናቄ የተነሳ ነው።

አቶ ጌጡ ከክፍለ ከተማው ዶሮዎች፣ መኖ እና የዶሮ ማስቀመጫ ተረክበዋል። “አሁን ባገኘሁት ድጋፍ ደስተኛ ነኝ፤ ያለኝን ልምድ ተጠቅሜ የቤተሰቤን ሕይወት እቀይራለሁ” ሲሉ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ።

የአቶ ጌጡ ታሪክ የብዙዎች ታሪክ ነጸብራቅ ነው። የስድስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሀብታሙ ታደሰም በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተው ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ።

ለእሳቸውና ለልጆቻቸው እንቁላል መመገብ ቀደም ሲል “የቅንጦት” ያህል የሚከብድ ነበር። ዛሬ ግን በጓሯቸው የሚያረቧቸው ዶሮዎች ለልጆቻቸው ገንቢ ምግብን፣ ለቤታቸው ደግሞ ተጨማሪ ገቢን ይዘው መጥተዋል።

ወይዘሮ ትግስት ሰለሞንም ቢሆኑ “ልጆቼን በአግባቡ ለመመገብና ያልተገባ ወጪን ለመቀነስ ትልቅ ዕድል ነው” በማለት የከተማ ግብርናው በቤት እመቤቶች ላይ የፈጠረውን እፎይታ ይገልጻሉ።

በክፍለ ከተማው ከተደረገው የአስር ሽህ ዶሮዎች፣ መኖ እና ሼዶች ድጋፍ ባሻገር ባለሙያዎቹ ቤት ለቤት እየሄዱ ሙያዊ ድጋፍ በማድረግ ዜጎች በራሳቸው ጓሮ የራሳቸውን ብልጽግና ዕውን እንዲያደርጉ መደላድል እየተፈጠረ ነው።

ይህ በአዲስ አበባ ከተማ እየተተገበረ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ በከተማ አስተዳደሩ በጀት እና በልበ ቀና ባለሀብቶች ድጋፍ በቦሌ ክፍለ ከተማ ብቻ 1700 የሚደርሱ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

እንደ አቶ ጌጡ ያሉ ዜጎችም በክፍለ ከተማው በተደረገላቸው ድጋፍ የተነሳ ከእንግዲህ የሚያስቡት ስለ ቤት ኪራይና የዕለት ጉርስ ብቻ ሳይሆን በጓሯቸው ባገኙት ትሩፋት ራሳቸውን ችለው ለሀገር ብልጽግናም ስለመትረፍ ጭምር ሆኗል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review