የኢትዮጵያ የቡና ሀብትና ልዩ ልዩ የተፈጥሮ መስህቦች በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኙ የማስተዋወቅ ስራ በትኩረት መሰራት እንዳለበት የመገናኛ ብዙኃን አባላት ገለጹ።
በቱሪዝም ሚኒስቴር በተዘጋጀ የቡና ቱሪዝም የትውውቅ ጉዞ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፋ ዞን፣ ዴቻ ወረዳ በቦንጋ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ማንኪራ ገጠር ቀበሌ ጉብኝት ተካሄዷል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የከፋ ዞን የቡና ጥብቅ ደን፣ “እግዚአብሔር ድልድይ” ተብሎ የሚጠራውን የተፈጥሮ ድልድይ እና ሌሎች የቡና አምራች አካባቢዎችን እና የተፈጥሮ ፀጋዎችን ተዟዙረው ተመልክተዋል።

የከፋ ዞን የቱሪዝም ባለሞያ አቶ ወንድሙ ማሞ ቡና ከመጠጥነትና ከንግድ ጥቅም በላይ የቱሪዝም መስህብ መሆኑን ገልፀው፣ የአካባቢው ማህበረሰብ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የከፋ ማህበረሰብ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ንክኪ ዙሪያ ያለው የታሪክና የባህል ልምድ ለዚህ ሀብት ቀጣይነት ትልቅ ሚና እየተወጣ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በክልልና በሀገር ደረጃ የኢትዮጵያ የቡና ታሪክና የከፋ ዞን የተፈጥሮ ፀጋ ለዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በተገቢው መልኩ የማስተዋወቅ ስራ መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
በካስዬ ማንጉዳ