ከበዓላት ባሻገር

You are currently viewing ከበዓላት ባሻገር

“መረዳዳት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል መስራት ይገባል”

የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪ ገብሬ ይንቲሶ (ፕ/ር)

በኢትዮጵያ ‘መስጠት አያጎድልም’፤ ‘ያለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም’ የሚሉ በማህበረሰቡ ዘንድ ስጦታ ማበርከትን፣ መደጋገፍንና  በጎ  ማድረግን የሚያበረታቱ አባባሎች አሉ። በሀይማኖታዊ አስተምሕሮውም ስጦታ ወይም መስጠት ትልቅ  ስፍራ የሚሰጠው መልካም ተግባር ነው፡፡

ያለንበት ወቅት ደግሞ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት (የገና በዓል) የሚከበርበት ነው። የገናን በዓል ስናነሳ ደግሞ ዋነኛ መለያው ስጦታ ማበርከት ነው፡፡ የእምነቱ አባቶች አስተምህሮ እንደሚያሳየው፣ የገና በዓል አንድም የሰው ልጅ ህግን በመተላለፉ ከገባበት ኃጢያትና ባርነት ነፃ ለማውጣት ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት ነው፡፡ ሌላው ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ ከሩቅ ምስራቅ የመጡ የጥበብ ሰዎች (ሰብዓ ሰገል) እጅ መንሻ ወርቅ እና ዕጣን ከርቤ ስጦታ አበርክተዋል፡፡ በዚህ መነሻነትም በገና ሰሞን ስጦታ ማበርከትና መለዋወጥ የተለመደ ነው፡፡

ስጦታ በኢትዮጵያውያን ባህል የቆየና የተለመደ ባህል ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይ በበዓላት ሰሞን አቅም የሚያንሳቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በዓልን በደስታ እንዲውሉ ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ የተለያዩ ስጦታዎችን ማበርከት እየተለመደ መጥቷል፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ሁጂራ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ማዘር ትሬዛ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳቸውን ጨምሮ አምስት የቤተሰብ አባላትን በሳምንት ሁለት ቀን “ሰንደይ ማርኬት” እየሰሩ በሚያገኙት ገቢ የቤት ኪራይ፣ የቤት ፍጆታና የልጆች የትምህርት ወጪ በመሸፈን እየኖሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሚባል እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ትዕግስት፣ ከዚህ ቀደም በተለይ በበዓል ወቅት ዶሮም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች መግዣ የሚሆን አቅም አጥተው በራቸውን ዘግተው ደስታ ርቋቸው ያሳልፉ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት በማዕድ ማጋራት በሚደረግላቸው ድጋፍ በዓልን በደስታ ማሳለፋቸውን ይናገራሉ፡፡ ለ2018 ዓ.ም አዲስ ዓመት ለበዓል ማሳለፊያ አንድ ሊትር ዘይት፣ 5 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ አንድ ኪሎ የአተር ክክ እና አንድ ኪሎ ምስር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ በዓላት ዶሮ እና እንቁላል ጭምር ድጋፍ አግኝተዋል፡፡ በዚህም ልጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን “ምን አበላቸዋለሁ” ብለው ሳይጨነቁ ደስተኛ ሆነው ማሳለፋቸውን ገልጸው እንዲህ ዓይነት ያለው ለሌላው የማካፈልና የመተጋገዝ ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በዚያው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ የሺ ሽኩርም እሳቸውን ጨምሮ አምስት የቤተሰብ አባላትን ያስተዳድራሉ። ኑሯቸውም ከእጅ ወደ አፍ የሚባል እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በበዓል ሰሞን ሲኖራቸው ዶሮና ሌሎች የቤት ውስጥ ፍጆታዎችን አሟልተው፤ ሳይኖራቸው ደግሞ እንደሌላው ጊዜ ራሳቸውን አሳምነው በባዶ ቤት ያሳልፉ እንደነበር ያነሳሉ፡፡ በማዕድ ማጋራት የሚያገኙት ድጋፍ በዓልን ሳይጎድልባቸው ከቤተሰባቸው ጋር ተደስተው እንዲያሳልፉ እንዳገዛቸው ተናግረዋል። “ድጋፉ  አስደሳች ነው፤ ተመስገን ነው የምለው፤ ከእኛም የባሱ፣ መንቀሳቀስ የማይችሉ፣ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው፣ አልጋ ላይ የሚውሉ አቅመ ደካሞችን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ ድጋፉ መጠናከር እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ ስጦታ ምንድን ነው? የስጦታና መደጋገፍ ባህል ፋይዳው እስከምን ድረስ ነው? እንደ አዲስ አበባ ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ ስጦታ ባህል እንዲሆን ምን እየተሰራ ነው? ስንል ዳሰሳ አድርገናል፡፡

የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪው ገብሬ ይንቲሶ (ፕ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ “ስጦታ አንድ ሰው ለሌላ ሰው ወይም ወገን ያለ ክፍያ፤ መልስ ሳይጠብቅ በነፃ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡ ስጦታውም ዕቃ፣ ገንዘብ፣ ጊዜና የተለያየ ሀብትና ንብረት ሊሆን ይችላል፡፡ ስጦታ በግለሰብ ወይም በድርጅትም ሊሰጥም ይችላል፡፡ ስጦታ ፍቅርንና ቸርነትን ለመግለፅ ይደረጋል፡፡ በተለይ ያለው ለሌላው በሚሰጥበት ጊዜ አብሮነትን ያጠናክራል”፡፡

ባህላችንን በደንብ ስለማናየው እንጂ በሀገራችን የዳበረ የመስጠት ባህል እንዳለ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪው ገብሬ (ፕ/ር) ያነሳሉ፡፡ “ለልጆች ስጦታ ማበርከት፣ በሀዘንና ደስታ ጊዜ፣ የታመመን ሰውና ዘመድ ለመጠየቅ ሲሄድ በባዶ እጅ ሳይሆን የተለያየ ስጦታ በመያዝ ነው፡፡ በቤተ እምነቶች በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በገና በዓል ስጦታ ማበርከት በተለይ በከተሞች ዘንድ እየተለመደ መጥቷል፡፡ በእስልምና እምነት በበዓል ወቅት ፆም ሲፈታ መልካም ማድረግ (ሱና) በፈጣሪ ዘንድ የተወደደ ተደርጎ ይወሰዳል”፡፡

በየብሔረሰቡም ስጦታ ማድረግ የተለመደ እንደሆነ የሚያነሱት የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪው ገብሬ (ፕ/ር)፣ እሳቸው በወጡበት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል (ዲሽታ ጊና) በሚከበርበት ወቅት አስቀድሞ ከ10 ወይም 15 ቀናት በፊት ሰዎች ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል ያለው ለሌለው ድጋፍ ማድረግ ይጠቀሳል፡፡

ስጦታ የሚያስገኘው ጥቅም ዘርፈ ብዙ እንደሆነ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪው ገብሬ (ፕ/ር) ያነሳሉ። “በመስጠት ደስታና እርካታ ይገኛል። ወዳጅነት ይጠናከራል፡፡ ህይወት ይታደሳል፡፡ ሰጪው ብቻ ሳይሆን ተቀባዩም ችግሩ ይቀረፍለታል፤ ክብርና ደስታም ይሰማዋል፡፡ ስጦታ ሲደረግ የሚያይ ታዛቢም እውቀትና ልምድ ይሆነዋል፡፡ ‘ለካስ እንደዚህ ማድረግ ይቻላል’ የሚል ስሜት ይፈጥርበታል”፡፡

“ስጦታን ባህል ስናደርግ ማህበራዊ ትስስርና  መተባበር እየተጠናከረ ይሄዳል።  መተሳሰብና መደጋገፍ ይኖራል።  በተቋማት የሚደረገው ስጦታም በተደራጀ  መልክ ድጋፍ ለሚፈልጉ ወገኖች ተደራሽ ለመሆን ይረዳል።”  ብለዋል፤  የሶሻል  አንትሮፖሎጂ ተመራማሪው ገብሬ (ፕ/ር)። 

እንደ ከተማ ምን እየተሰራ ነው?

በአዲስ አበባ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ አስራት ንጉሴ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ “በክረምትና በበጋ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ አሰራር በመዘርጋት እና ማህበረሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። በዚህም የበርካታ ዜጎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ማቃለል ተችሏል”፡፡

በበዓል ሰሞን ከሚደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል ማዕድ ማጋራት አንዱ ሲሆን ዜጎች በተለይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙት እንደ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በዓልን በፈገግታ ተሞልተው ተደስተው እንዲያሳልፉ አስችሏል፡፡ በዚህ መርሃ ግብርም ባለፉት ሰባት ዓመታት በድግግሞሽ 7 ሚሊዮን የከተማዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ የህብረተሰብ ተሳትፎ እና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወይዘሮ አስራት እንደገለፁት፣ እንደ ማዕድ ማጋራት ያሉ የበጎነት ስራዎች ለህብረተሰቡ ያላቸው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን የሚቸገሩ አቅመ ደካሞች፣ የሀገር ባለውለታዎችና አካል ጉዳተኞችና እጅ ያጠራቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ማቃለል አስችሏል። ‘የሚደግፈኝ ወገን አለኝ’ ብለው ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓል፡፡

ማህበራዊ መስተጋብርን በማጠናከር፣ ማህበራዊ ፍትህን በማረጋገጥ፣ የወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴትን በማጎልበት፣ ማህበረሰብ በመንግስት ላይ  ያለውን እምነት በማሳደግ  ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ 

ማዕድ በማጋራት ወይም በሌላ መልክ በሚሰራው የበጎነት ስራ ድጋፍ የሚደረግላቸው ብቻ ሳይሆን ለጋሾችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ወይዘሮ አስራት ይናገራሉ፡፡ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ማዕድ በማጋራትና በተለያየ መልኩ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ትስስር፣ መተማመንና መቀራረብ እያደገ ይመጣል፡፡ እውቅናና ምስጋና ያገኛሉ፤ ድርጅቶች ምርታቸውን መሸጥ ይችላሉ። በማህበረሰቡ ውስጥ “የኔ ተቋም ነው” የሚል የባለቤትነት ስሜት ይፈጥራል። ስማቸውና የድርጅታቸው ማንነት (ብራንድ) ከፍ ይላል፡፡

የአዲስ አበባ ህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ርዕይ በጎ ፈቃደኝነት ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ተገንብቶ ማየት እንደሆነ ያነሱት ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ አስራት፣ በጎ ፈቃደኝነትን ባህሉ ያደረገ ማህበረሰብ ሲኖር በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች ያሉ ጉድለቶች እየተሞሉ፣ ማህበራዊ ፍትህ እየተረጋገጠ ይሄዳል፡፡

ማዕድ ማጋራትና መሰል የስጦታ ተግባራት ወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት፣ ማህበራዊ መስተጋብር እንዲያድግ አድርጓል፡፡  በጎ ፈቃደኝነት ባህል  ያደረገ ትውልድ የሚገነባበት  ዕድል ተፈጥሯል፡፡  በጎነት በፖለቲካው መስክ የበጎነት ስራዎች መረዳዳት፣ መካፈል፣ መደጋገፍና አብሮነትን  በማጠናከር ሰላማዊና የተግባባ ማህበረሰብ በመፍጠር አስተዋፅኦ  እያበረከቱ  ይገኛሉ፡፡

መደጋገፍና መተጋገዝ የኢትዮ ጵያውያን የቆየ ባህልና እሴት ነው፡፡ በሀይማኖት አስተምህሮዎችም የሚደገፍ በጎ ተግባር ነው፡፡ በጎነት ባህል እንዲሆን መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎችን፣ ገፅ ለገፅ በሚኖሩ መድረኮችን በመጠቀም ስለበጎነት ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር እየተሰራ ይገኛል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ የተሻለ እንቅስቃሴ ለሚያደርጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች እውቅና በመስጠት የበለጠ እንዲሰሩ የማነሳሳትና ሌሎች ትምህርት ወስደው እንዲሳተፉ በማድረግ በጎነት ባህል እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝ ወይዘሮ አስራት ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ቀደም ብሎ የፀደቀውና ባለፈው ዓመት ተግባራዊ መሆን የጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የማህበራዊ ኃላፊነት አሰራር ደንብ ቁጥር 161/2016ን በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ስራ ለማስገባት፣ ዜጎች በግልና በተደራጀ መንገድ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉና ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል በደንቡ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ባህል እንዲሆን ምን መሰራት ይኖርበታል?

በበዓል ሰሞን የሚደረጉ የማዕድ ማጋራትና መሰል ስጦታዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው የሚሉት የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪው ገብሬ ይንቲሶ (ፕ/ር)፣ የስጦታና መሰል የበጎነት ስራዎች ባህል እንዲሆኑ የቀደመውን ባህላችንን ወደኋላ ዞር ብሎ መፈተሽ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ በተለይ በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ ስጦታ የሚሰጠው ‘በበዓል ሰሞን ብቻ ነው? ወይስ በሌላው ቀንም ይደረጋል’ የሚለውን መለስ ብለን ብናይ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን እናገኛለን። ለምሳሌ በአሪ ብሔረሰብ በበዓል ወቅት ከሚደረገው በተጨማሪ በሌሎች መደበኛ ቀናትም በጎ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ አንድ ሰው መሬት ኖሮት መሬቱን የሚያርስበት በሬ ከሌለው የበሬ ጉልበት በነፃ ይሰጣል፡፡ መሬትና ዘርም ይሰጣል፡፡

ስጦታ በበዓል ቀን ብቻ የምናደርገው ሊሆን አይገባም፡፡ በበዓል ወቅት ከሚደረገው የማዕድ ማጋራትና ሌሎች ስጦታዎች በተጨማሪ ባህላችንም ውስጥ ስላለ፤ በሌላውም ቀን፣ አቅም ለሚያንሳቸው ወገኖች ድጋፍ ማድረግና ራሳቸውን የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር መስራት ይገባል። በዚህ ረገድ ከታች ጀምሮ ልጆች ጥሩ ስብእና ተላብሰው እንዲያድጉ ማስተማር ይገባል፡፡ ስለ መልካምነት፣ ቸርነት፣ ልግስና፣ ትብብር ማስተማር ያስፈልጋል።ይህን ማድረግ ሲያድጉ በጎ ማድረግን እየተላበሱ፣ መደጋገፍና መተባበርን ባህል እያደረጉት እንዲሄዱ ያደርጋል፡፡ በማህበረሰብ መካከል ያለው ትብብርና ትስስርም ይጠናከራል፡፡ በማህበረሰብ  ዘንድ ያሉትን ነባር  እሴቶች በማጠናከር ስጦታ ወሳኝ የመረዳዳት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ መስራት እንደሚገባ የሶሻል አንትሮፖሎጂ ተመራማሪው አስገንዝበዋል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review