እየተሰሩ ያሉ የከተማ ልማት ስራዎች በከተሞች መካከል ትብብርንና የመልማት ፉክክርን የፈጠሩ መሆናቸውን የኢፌድሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን ያስታወቀው በክረምት የበጎ ፈቃድና የገጠር ሞዴል መንደሮችን ስራ አፈፃፀም አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውን የኮሪደር ልማት ስራ በክልል ከተሞች በማስፋፋት የዜጎችን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢፌድሪ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል።
ከመዲናዋ ባለፈ በ76 ከተሞች ላይ የኮሪደር ልማት ስራን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በቅርቡ የተከናወኑ የገጠር ሞዴል መንደር ግንባታዎችም የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ምቹነት ያሳደጉ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም፤ እየተሰሩ ያሉ የከተማ ልማት ስራዎች በከተሞች መካከል ትብብርንና የመልማት ፉክክርን የፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት አምስት አመታት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካቶችን ተደራሽ ያደረገ ስራ ማከናወኑን ያነሱት ሚኒስትሯ፤ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቱሉ አራራ ከተማ ሞዴል መንደሮችን ገንብተው ለተጠቃሚዎች ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል።
በከተሞች እየተከናኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የዜጎችን የኑሮ ምቹነት ከማላበስ ባለፈ ተጨማሪ የስራ እድልን የፈጠሩና የስራ ባህልን የቀየሩ ስለመሆናቸውም በመግለጫው ተመላክቷል።
በታምሩ ደምሴ