የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ኪነ ጥበባዊ መሰናዶዎች

በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የሃሳብ እና መጽሐፍ ውይይት፣ ሙዚቃ፣ የፎቶ ግራፍ እና የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡

ፌስቲቫል

ኢትዮጵያዊ ምግቦች የሚቀርቡበት ፌስቲቫል ክፍት ሊሆን ነው። “ጋስትሮኖሚ” የተሰኘውን ይህን ፌስቲቫል የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ጎልደን ግሩፕ ሆስፒታሊቲ ከተሰኘ ድርጅት ጋር አዘጋጅቶታል፡፡ ዛሬ እና ነገ ክፍት የሚሆነውን ይኸን ፌስቲቫል የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፌስቲቫሉ የተዘጋጀው ደግሞ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሆነ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ኤፍ ኤም 96.3 ራዲዮ ገልጸዋል፡፡

መጽሐፍት

“የፍልስፍና ሐሳቦች” የተሰኘው የትርጉም መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ ይህ መጽሐፍ ስድስት መጻሐፍትን  በአንድ ጥራይዝ የያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የመጽሐፉ ተርጓሚ ሙሉቀን ታሪኩ ሲሆን አርትኦቱ የተሰራው ደግሞ በፋሲካ ግዛውና አማረ ብርሃኑ ነው፡፡

በተጨማሪም በደሳለኝ ከበደ (ኢ/ር) የተጻፈው “የሪል እስቴት ግብይት” መጽሐፍ ታትሞ ለንባብ በቅቷል። ደራሲው ከዚህ ቀደም “ሪል እስቴት ኢንቨስትመንት” የሚል መጽሐፍ ለንባብ ለአንባቢያን ማድረሱ ይታወሳል። አዲሱ መጽሐፍ ለቤት ገዢዎች፣ ለግብይት ወኪሎች (ኤጀንቶች)፣ ደላሎች፣ ለሻጮች እና ለቤት አልሚዎች ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሪል እስቴት ገበያ ውስጥ የግብይት ጥረቶችን ውጤታማ ለማድረግ የሚረዱ አዳዲስ ስልቶችን እና ውጤታማ ቴክኒኮችን ያያዘ ነው ተብሏል። በተጨማሪም የግብይት አካሄዶችን ውጤታማ ለማድረግ፣ የሽያጭ ዘዴን እና የአልሚነት ፕሮጀክቶችን ለማሻሻል፣ ገዢዎችንም ለመሳብ  የሚረዱ ሃሳቦችን ማካተቱ ተነግሯል፡፡

በሌላ መረጃ “ሸግዬ ሸጊቱ” የተሰኘው መጽሐፍ ለ3ኛ ጊዜ ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡ በሚካኤል አስጨናቂ የተጻፈውና ተወዳጅነትን ያተረፈው ይኸው መጽሐፍ የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ  ነው፡፡

የሃሳብ ውይይት

በዛሬው እለት “የሃሳብ እና መፅሐፍ” ውይይት መድረክ ይካሄዳል፡፡ ውይይቱ ስለ ቀለም አይነት እና ትርጓሜ፣ ስለ ቀለም ፅብረቃ እና በስነ-ልቦና ላይ ስለሚያደርሱት ልውጥውጥ ስሜቶች፣  ስለ መልክ እንዲሁም ስለ ምልክቶች በተጨማሪም ስለገፅታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡

የውይይት መነሻ ሃሳብ የሚያቀርቡት ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ (ቀለም ፊሎሶፊ) እና  ሰዓሊ ሶሎሜ ጌታቸው ናቸው፡፡ ውይይቱ የሚካሄደው 4 ኪሎ ኢክላስ ህንፃ ዋልያ መጽሐፍት  አዳራሽ ሲሆን ከሰዓት 8:00 ሰዓት ጀምሮ መርሃ ግብሩ መካሄድ ይጀምራል ተብሏል።

የፎቶ ግራፍ አውደ ርእይ

“በቅጽበቶች መካከል” የተሰኘው የስእል አውደ ርእይ በእይታ ላይ ነው። አሸናፊ የማነ፣ ርብቃ ሲሳይ እና ልዑል መኮንን በጋራ ያዘጋጁት ይህ አውደ ርእይ የተጀመረው ባሳለፍነው ረቡዕ እለት ነው። አውደ ርእይው እስከ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን እየታየ የሚገኘው  በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚገኛው ፈንድቃ የባህል ማእከል ነው።

ሙዚቃ

ድምጻዊ ብዙአየሁ ደምሴ አዲስ የሙዚቃ ስራ ለአድማጭ ተመልካች ሊያደርስ ነው፡፡ ቀደም ሲል በሰራቸው በርካታ ሙዚቃ ስራዎች ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምፃዊ ብዙአየሁ ደምሴ  አሁን ደግሞ “መሽቶ ነጋ” የተሰኘ ሙዚቃ ወደ ህዝብ ለማድረስ ዝግጅቱን መጨረሱ ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ቀደም “ሳላይሽ” የተሰኘ አልበሙን ለህዝብ ያደረሰው ድምፃዊ  አሁን ደግሞ ይኸን አዲስ ነጠላ ዜማውን በናሆም ሪከርድስ አማካኝነት ለህዝብ እንደሚያደርስ ተገልጿል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review