የአዲስ አበባ ከተማ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር የኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማነትና ተግዳሮቶችን በጥናት ለመለየት የሚያስችል የጥናት ውል ስምምነት አደረገ።
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር) አማካኝነት ተፈርሟል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
አስተዳደሩ ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ያስቻሉ ስኬቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።
በመሆኑም በሁለቱ ተቋማት የተደረሰው ይህ ስምምነት ይህንኑ ተግባር ይበልጥ የሚያጠናክር እና ከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ የታቀዱ እቅዶችን ዳር ለማድረስ የሚያግዝ መሆኑም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ እንደ ኢትዮጵያ ታምርት የመሰሉ የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው ይህም መንግስት በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል ብለዋል።
በዚህም እንደከተማ በዘርፉ አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ያነሱት ምክትል ከንቲባው፣ የተጀመሩ ለውጦችን ይበልጥ ለማጠናከርና እንደከተማም ብሎም እንደሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችል ጥናት ለማካሄድ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ጋር ተፈራርመናል ብለዋል።
ስምምነቱ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮው በመደበኛነት ከሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ በተሻለ በሳይንሳዊ ጥናት የተደገፈ እና በተጨባጭ የኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማነትና ተግዳሮቶችን ለመለየት እንደሚያስችል የገለፁት አቶ ጃንጥራር አባይ የዘርፉን ፍኖተ ካርታ እና ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀት ጭምር የተካተተበት መሆኑን አብራርተዋል።
ጥናቱ በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚካሄድ የጠቆሙት የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ደረጀ እንግዳ (ዶ/ር)፣ ስራው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በጥራት በማከናወን ለዘርፉ እድገት እንደተቋም የድርሻቸውን እንደሚያበረክቱ ገልፀዋል።
በሁለት ቡድን የተዋቀረው የጥናት ቡድን 52 አባላትን የያዘ መሆኑ የስምምነት ፊርማ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በታምሩ ደምሴ