AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም

መንግስት በቅርቡ ከከፍተኛ ባለስልጣናት እስከ ታችኛው የሴክተር መዋቅር ድረስ የጀመረው የፀረ-ሌብነት እና ህገ-ወጥነትን የማፅዳት ዘመቻ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍን አግኝቷል።
ይሁን እንጂ “መንግስት ብቻውን ሌብነትን ማጥፋት አይችልም ያሉት ነዋሪዎቹ፣ ህብረተሰቡ ጉቦ ከመስጠት መቆጠብ፣ አመለካከቱን መቀየር እና ሌቦችን በድፍረት ማጋለጥ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

መንግስት የጀመረውን የፀረ-ሙስና እርምጃ አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያሉባቸውን ስጋቶች እና መወሰድ አለባቸው ያሏቸውን የቀጣይ መፍትሄዎች ለኤ ኤም ኤን አጋርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ ገረመው ገብረወልድ፣ ሌብነቱ እንዲህ እንዲሰፋ ያደረገው ‘ማንም አይነካኝም’ በሚል የዳበረ የድፍረት ስሜት መሆኑን አንስተዋል።

አሁን ግን ቢዘገይም መንግስት ከላይኛው መዋቅር ጀምሮ ህግን ተከትሎ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ሳላደንቅ አላልፍም ነው ያሉት።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ፍቃዱ ደጀኔ፣ ከፍተኛ የመንግስት ተቋማት ላይ የጀመረው ስራ የሚደነቅ እንደሆነና እርምጃው ወደ ታችኛው ሴክተሮችም መውረዱ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ኢፋ ተሬሳ የተባሉት የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ፣ ሀገሪቷ እስከ አሁን ሳታድግ ወደኋላ የቀረችው በሌብነት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ ትክክለኛ እና አግባብነት ያለው እንደሆነ አመላክተዋል።
የሙስናው ዋነኛ አንቀሳቃሽ ባለስልጣኑ ወይም ባለሙያው ብቻ ሳይሆን፣ ጉዳዩ እንዲፈጸምለት ገንዘብ የሚሰጠው ግለሰብ እና በመሃል የሚያገናኘው ደላላ ጭምር መሆኑን ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ።

አቶ አብረሃም በቀለ እና አቶ ጥበቡ ወልደ ጨርቆስ የተባሉት የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ በሙስና ወንጀል ሰጪውም ተቀባዩም አንድ ናቸው በማለት ገልጸዋል።
ህብረተሰቡም ጉቦ ከመስጠት መቆጠብ እና ካልሰጠሁ አይፈጸምልኝም የሚለውን ብልሹ አስተሳሰብ መስበር አለበት በማለት ይመክራሉ።
ህብረተሰቡ ሌቦችን እንደ ጀግና ከማየት ወጥቶ ወደ ማጋለጥ ሊሸጋገር ይገባል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ መንግስትም ለጥቆማ ምቹ የሆኑ አሰራሮችን ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል።
ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል የሚለው ብሂል ማብቃት እንዳለበት እና በአካባቢያችን ያሉ ሌቦችን ወደ ህግ በማቅረብ ተጠያቂ ማድረግ የዜግነት ግዴታችን ነው ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ