AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም

ሌብነት እና ሙስና የሀገርን እድገት የሚያቀጭጩ ፣ የሕዝብን እምነት የሚሸረሽሩ እና የማኅበራዊ ፍትሕ መሠረትን የሚያናጉ አደገኛ ደዌዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ምዕራፍ የከፈተው የመደመር ፍልስፍና፣ ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ የጋራ ሀብትን በፍትሐዊነት እና በአግባቡ ማስተዳደርን ቀዳሚ መርሑ አድርጎ እየሰራ ነው።
የመደመር መንግሥት ከተፈጥሮው እና ከእሴቱ ጋር ፈጽሞ የማይስማማውን ሌብነትንና ሙስናን በጽኑ የሚጸየፍ፣ እውነተኛ ሌብነት ጠል መንግሥት መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል። ከሰሞኑ የህብረተሰቡን ጥቆማና አቤቱታ መነሻ በማድረግ በሌብነት ላይ ወሳኝ እርምጃ በመውሰድም ቁርጠኝነቱን አረጋግጧል።
የመደመር ፍልስፍና ዋና ማዕከል የጋራ ብልጽግናን ማረጋገጥ ነው። የጋራ ብልጽግና ደግሞ ያለ ሀብት ምዝበራ እና ያለ ፍትሕ መጓደል የሚሳካ ግብ ነው።
የመደመር መንግሥት ሀገራዊ ሀብት ጥቂቶች በብቸኝነት የሚዘርፉት ሳይሆን የሁሉም ዜጋ የጋራ ውርስ እና የመጪው ትውልድ ተስፋ መሆኑን ያምናል።
በመሆኑም የሕዝብን ሀብት ለመጠበቅና ለታለመለት የልማት ዓላማ ብቻ እንዲውል ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የመደመር ፍልስፍናው የሕልውና ጉዳይ ነው።
ሌብነትን መታገል እና ሀብትን በአግባቡ ማስተዳደር በመደመር እሳቤ ውስጥ አማራጭ ሳይሆን የዕለት ተዕለት አሠራር መመሪያ ሆኖ ነው እየተተገበረ የሚገኘው። የመደመር መንግሥት እያካሄደ ያለው የጸረ-ሙስና ትግል መዋቅራዊ እና ጥልቅ መልካም አስተዳደርን የማስፈን እርምጃ ነው።
የፀረ ሌብነት ትግሉ የሕግ የበላይነትንም ማረጋገጥ ሲሆን አሠራሮችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማስደገፍ የሌብነት ቀዳዳዎችን የሚደፍን፣ የግልጽነት እና የተጠያቂነት ሥርዓትን የሚያሰፍን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል።
መንግሥት ሌብነትን ከሥሩ ነቅሎ ለማስወገድ የያዘው ቁርጠኝነት የሚያሳየው የጸረ-ሙስና እንቅስቃሴው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ሀገርን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት የተወጠነ መሆኑን ነው።
የጋራ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጉዞ ስኬታማ የሚሆነው ሀገራዊ ሀብትን ከምዝበራ በመጠበቅ እና ለልማት በማዋል ብቻ እንደሆነ በጽኑ የሚያምነው የመደመር መንግሥት ሌብነትን የመታገል ቁርጠኝነቱን እየወሰዳቸው ባሉ እርምጃዎች አሳይቷል።
ሌብነትን የመጸየፍ አቋም እያንዳንዱ የመንግሥት መዋቅር እና ሕዝብ የሚጋራው ባህል ሆኖ እንዲጎለብትም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሁሉምን ተሳትፎ ይፈልጋል።
በታደሰ ሽፈራው