የአውሮፓ አሸናፊዎች የሚፋጠጡበት ታላቁ ግጥሚያ

AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም

የ2026 የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ዛሬ ይደረጋል።

የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ፓሪሰን ዠርማ እና የዩሮፓ ሊግ ባለድሉ አስቶንቪላን የሚያፋጥጠው ጨዋታ በኦስትሪያ ሬድ ቡል አሬና ይከናወናል።

ሁለት ተከታታይ የውድድር ዓመት የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ያሸነፈው ፓሪሰን ዠርማ ባለፈው ዓመት ቶተንሃም ሆትስፐርስን በመርታት ሱፐር ካፑን ማሸነፉ ይታወሳል።

ይህን ድል ዛሬም ከደገመ ከአያክስ ፣ ሚላን እና ሪያል ማድሪድ በመቀጠል የአውሮፓ ሱፐር ካፕን በተከታታይ ያሸነፈ አራተኛው ክለብ ይሆናል።

አስቶንቪላም ለዚህ ዋንጫ አዲስ አይደለም ፤ እኤአ በ1982 በድምር ውጤት ባርሰሎናን 3ለ1 በማሸነፍ ዋንጫውን የግሉ አድርጓል።

ፓሪሰን ዠርማ እና አስቶንቪላ የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ላይ ሁለት ጊዜ ተገናኝተዋል።

በ2024/25 የውድድር ዓመት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ላይ ተገናኝተው ፓሪሰን ዠርማ በፓርክደ ፕሪንስ 3ለ1 ሲያሸንፍ አስቶንቪላ በቪላ ፓርክ 3ለ2 ረቷል።

የፓሪሱ ክለብ በድምር ውጤት 5ለ4 በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜ መቀላቀሉ ይታወሳል።

የዛሬውን ተጠባቂ ጨዋታ ሶማሊያዊው ዋና ዳኛ ኦማር አርታን ይመራዋል።

የ34 ዓመቱ ወጣት አልቢትር የ2026ቱን ዓለም ዋንጫ ለመዳኘት ወደ አሜሪካ እንዳይገባ በመከልከሉ ነበር የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ለማበረታታት ይህን ዕድል የሰጠው።

በሬድ ቡል አሬና የሚከናወነው ጨዋታ ምሽት 4፡00 ላይ ይጀምራል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review