ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ፣ በፀሐይና በብርድ ውስጥ በጎዳና ላይ በጉልት ንግድ ይተዳደሩ ለነበሩ እናቶች፤ ዘመናዊ የንግድ ሼድ ሰርተንና አስፈላጊውን ግብዓት ሁሉ አሟልተን አስረክበናል ብለዋል፡፡
እነዚህ እናቶች ለረጅም ዓመታት ፀሐይና ብርድ እየተፈራረቀባቸዉ ፣ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ ጤናቸው እየታወከም ቢሆን ለኑሮ ሲሉ በሜዳ ላይ ጉልት እየቸረቸሩ ልጆቻቸውን ያስተማሩና ቤተሰብ ያስተዳደሩ ብርቱ እናቶች ናቸው። ዛሬ የሚገባቸውን ክብር አግኝተውና ተደስተው በማየታችን እኛም ደስ ብሎናል ብለዋል፡፡
በከተማችን በስፋት የተገበርነውን የኮሪደር ልማት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የቀድሞውን የጉሊት ንግድ በማንሳት የገነባነውን ዘመናዊና ደረጃውን የጠበቀ የንግድ ሼድ በዛሬው ዕለት አስረክበናቸዋል።
በተጨማሪም የምርት አቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ከላፍቶ ገበያ ማዕከል ጋር ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ተደርጓል። የአካባቢው ማህበረሰብም ከዚህ ፅድት ካለ፣ ሰፊ የሚኪና ማቆሚያ ፣ ካፍቴሪያ እና በቂ የንፅህና ቤቶች ተሟልቶ ከተገነባለት የገበያ ስፍራ እና ከእነዚህን ጠንካራ እናቶች ምርታቸውን በመሸመት እንድታበረታቷቸው በአደራ ጭምር ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡
ልማታችን “ሰው ተኮር ነው” ስንል፣ ይህ ተግባር አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡