AMN ጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የእራሱን ታሪክ አሰንዶ ትናንት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ያሰናዳቸው ውድድር በበርካታ መለኪያዎቹ “እጅሽ ይባረክ” የሚያስብል ነው።
በተለይ የስታዲየሞቹ ጥራት አፍሪካ ውስጥ ነው ብሎ ለማመን እንደሚያስቸግር አሰልጣኞች ጭምር መስክረዋል። በሌሎች መስተንግዶም ቢሆን ፍፁም ነው ባይባልም ከወቃሾቹ ይልቅ ምስጋና አድራሾቹ ይበረክታሉ። ትናንት በፍፃሜው ዕለት የታየው ድራማ ግን ያሁሉ የአፍሪካን መልካም ገፅታ ገደል የከተተ ሆኗል።
አዘጋጇ ሞሮኮ እና ሴኔጋል ያከናወኑት የፍፃሜ ጨዋታ ግብ ለማሳየት እስከ ጭማሪ ደቂቃ ቢያስጠብቅም ድንቅ ፉክክር የታየበት ነበር።

በጨዋታው መደበኛው 90 ደቂቃ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃ ላይ ሞሮኮ ብራሂም ዲያዝ ላይ በተፈፀመ ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠ።
ፍፁም ቅጣት ምት ከመሰጠቱ ደቂቃዎች በፊት ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ከመረብ አሳርፈው ጥፋት ተሰርቷል በሚል ግቡ የተሻረባቸው ሴኔጋሎች ውሴኔውን መቀበል አልቻሉም።
ከዚህም አልፈው ሜዳ ለቀው እንዲወጡ የ43 ዓመቱ ወጣት አሰልጣኝ ፓፔ ቲያው ተነገራቸው። አሰልጣኙ ነገሮችን ከማረጋጋት ይልቅ በእንደዚህ አይነት ተግባር መሳተፉ “ፕሮፌሽናሊዝም” ያልገባው አስብሎታል።
ፓፔ ቲያው ሀገሩን ከዚህም በላይ ስኬታማ የማድረግ አቅም እንዳለው ቢነገርለትም የትናንት ምሽት ተግባሩ ግን ሌላ ገፅታ አላብሶታል።
ሳዲዮ ማኔ በዋና ዳኛው ዦን ጃኬ ንጋምቦ ውሳኔ ደስተኛ ባይሆንም ሜዳ ለቆ መውጣቱን ግን አልመረጠም። የቡድን አጋሮቹ እና አሰልጣኝ ቡድን አባላት ተረጋግተው ጨዋታው እንዲቀጥል አስማማ።
መልበሻ ክፍል ገብተው የነበሩ ተጫዋቾችንም ጠርቶ ጨዋታው እንዲቀጥል አደረገ። እንደ አጋጣሚ ብራሂም ዲያዝ ፍፁም ቅጣት ምቱን ሳይጠቀምበት ቀረ።

ሴኔጋልም በጭማሪ 30 ደቂቃ በፓፔ ጌይ ጉርም ግብ አስቆጥራ ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት ሆነች። የመጨረሻው የአፍሪካ ዋንጫው እንደሆነ ቀድሞ የተናገረው ሳዲዮ ማኔ በስነ ምግባር በተሞላ ተግባሩ ስሙን ዘላለማዊ አደረገ።
ድሮም በመልካም ተግባሩ የሚታወቀው እና ለበርካቶች አርአያ መሆን የቻለው የአልናስሩ ተጫዋች የበለጠ በበጎ እንዲታወስ ማድረግ ቻለ።
አሰልጣኙ ፓፔ ቲያው ግን በሞሮኮ አሰልጣኝ ጭምር “ለአፍሪካ እግርኳስ መጥፎ ምስል የሰጠ ተግባር” የሚል ትችት ለማስተናገድ ተገድዷል።
በትልቅ መድረክ ላይ ሳይሆን የመንደር ጨወዋታ ይመራ ይመስል ተጫዋቾቹን ከሜዳ ውጡ ማለቱ አሰልጣኙ በበጎ የማይታወስበት አንዱ ተግባሩ ሆኖ ይቀጥላል። ለአሁኑ ግን ለሁለተኛ ጊዜ የአህጉሪቱ ቁንጮ የሆኑበትን ድል እያጣጣመ ይገኛል።
በሸዋንግዛው ግርማ