AMN ጥር 14/2018
አዲስ አበባ ከተማ እያስመዘገበች የምትገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን ነው ሲሉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ከንቲባዎች ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአሕጉራዊ የተሞክሮ ልውውጥ እና የድርጊት መርሃ-ግብር ግምገማ አውደ ጥናት ተጠናቋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎችና የስራ ኃላፊዎች ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ: የዲጂታል የገቢ አሰባሰብ ስርዓት: የከተማዋን የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ሰዉ ተኮር ስራዎችን ተመልክተዋል።
በአዲስ አበባ የታዘቧቸው ተሞክሮዎች ለሀገሮቻቸው ትልቅ ትምህርት የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከተማዋ ግብር የምትሰበስብበትንና ተግባራትን የምታከናውንበትን መንገድ መመልከታቸውን ጠቅሰው ከዚህም ሰፊ ልምድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡
ያገኟቸዉን ተሞክሮዎች በከተሞቻቸዉ ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ያየነው የገቢ አሰባሰብ ስርዓትና ገቢ እንዳይባክን የሚደረጉ የፈጠራ ስራዎች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።
አዲስ አበባ ከተማ በሴት ከንቲባ በመመራት አስገራሚ ለውጥ ማምጣቷ በአፍሪካ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት አራዓያ የሚሆን ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሚካኤል ሂሩይ