AMN – ጥር 19/2018 ዓ.ም
የአፍሪካ መዲና እና የዓለም የዲፕሎማሲ መናኸሪያ የሆነችው አዲስ አበባ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተከትሎ የቱሪዝም ዘርፏ እያገገመ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል ከተማዋ የነበረባት የመሰረተ ልማት እጥረት እና የከተማ ጉስቁልና ተቀርፎ ዛሬ ላይ ለቱሪስቶች ቀዳሚ መዳረሻ መሆን መቻሏን ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቆይታ ያደረጉ የዘርፉ ባለሙያዎች እና ባለሀብቶች ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ለዘመናት የአፍሪካ የፖለቲካ ማዕከል ብትሆንም፣ የመንገዶች መጨናነቅ፣ የወንዞች መበከልና የቱሪስት መቆያ ስፍራዎች እጥረት የከተማዋ መለያዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መዲናዋን ከመሸጋገሪያነት ወደ ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻነት ቀይረዋታል።

በቱሪዝም ዘርፉ ከ16 ዓመታት በላይ የቆዩት አቶ ይታየው ምትኩ እንደሚሉት፣ ቀደም ሲል የነበረው የከተማዋ ገጽታ ለቱሪስቶች ምቾት የማይሰጥ ነበር።
ቱሪስቶች መጥተው የሚጎበኟቸው ቦታዎች ማነስ ቆይታቸውን ያሳጥረው እንደነበር የሚገልጹት አቶ ይታየው አሁን ግን ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት የተሰሩት አዳዲስ መዳረሻዎች ቱሪስቶች እንዲደሰቱና ቆይታቸውንም እንዲያራዝሙ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ይህ የመሰረተ ልማት ለውጥ የሆቴልና የኮንፈረንስ ቱሪዝሙን ክንፍ እንዲያወጣ ረድቶታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ፣ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለዘርፉ መነቃቃት ትልቁን ድርሻ እንደሚይዙ ተናግረዋል።

የኮንፈረንስ ቱሪዝም አሁን ላይ ትልቅ የከተማዋ ሀብት እየሆነ መጥቷል። ለአብነትም እንደ አድዋ ድል መታሰቢያ እና አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል ያሉ ፕሮጀክቶች እውን መሆናቸው መዲናዋን የኮንፈረንስ ማዕከል እንድትሆን አግዘዋል ያሉት ኮሚሽነር ሁንዴ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገድ እንደተቻለም አንስተዋል፡፡
በመዲናዋ በሆቴል ዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው፣ የከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት ለሆቴል ኢንዱስትሪው አዲስ ተስፋ መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም እንደ COP 32 ያሉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ ሆቴሎች በቂ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ተጠቁሟል።
የመዲናዋ ነባር የቱሪስት መስህቦች እንዲታደሱና አዳዲስ መዳረሻዎች እንዲለሙ መደረጋቸው፣ አዲስ አበባ ከተማን በአፍሪካ ተመራጭ የቱሪዝም መናኸሪያ እያደረጓት እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
በአስማረ መኮንን