AMN ጥር 19/ 2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በጀግኖች ልጆች መስዋዕትነት የፀናች፣ ከሀገር ውስጥ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት የሰላም ዋስትና መሆን የቻለች ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ሰዓት በአለማችን ጠንካራ ወታደራዊ ተቋም እየገነቡ ካሉ ሀገራት ተርታ አንዷ እየሆነች ትገኛለች ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ቀን በዓል አንዱ አካል የሆነው የበረራ፣ የዕጩ መኮንን እና የቴክኒሽያኖች ምረቃ መርሃ ግብር ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ብልጫ ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት፣ የበረራ ዲፕሎማና ዊንግ ከሠጡ እና ማዕረግ ካለበሱ በኋላ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ አየር ሀይል በበርካታ ድሎች እየደመቀና የላቀ የቴክኖሎጂ ስኬትን እያስመዘገበ የሚገኝ የአቭዬሽን ተቋም መሆኑን ሰሞኑን በተካሄደው አለም አቀፍ የአየር ትርኢት፣ የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም እና የአቭዬሽን ኤክክፖ ላይ በተግባር ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በበዙ ፈተናዎች ውስጥ እየፀና እና እየደመቀ በኢትዮጵያ ላይ ጦር የሰበቁ ጠላቶችን ክንድ በመደቆስና ቅስማቸውን በመሰባበር የሀገራችንን ሉአላዊነት ያፀና የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር ማዕከል የሆነ ታላቅ ተቋም ሥለመሆኑም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ አንስተዋል።
የዕለቱ ተመራቂዎችም ይህንን ኃያልነት አስጠብቀው በማስቀጠልና በስልጠና ያገኙትን አቅም በተግባር በማዋል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ ማሳሰባቸዉን የሃገር መከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያሳያል፡፡
“የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነፃነት እና የአንድነት ምልክት” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘው የአየር ኃይል ቀን ዛሬ በሚከናወኑ ቀሪ ዝግጅቶች የሚጠናቀቅ ይሆናል።