AMN – ጥር 20/2018 ዓ.ም
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በ27ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ሞቃዲሾ ገብተዋል።
ሚኒስትሩ በሞቃዲሾ ከአውሮፓ ኮሚሽን የዓለም አቀፍ አጋርነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሚስ ማይሪያም ፌራን ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።
የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ጋር በመተባበር በታዳሽ ኃይል ፣ በተቀናጀና ዘላቂ የኃይል አቅርቦት እና በዲጂታላይዜሽን ፕሮግራም በቅርቡ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡አጋርነቱ ቀጣይነት እንደሚኖረዉም ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ትብብርን ስለማሳደግ የመከሩ ሲሆን፣ የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ አካል የሆነውን የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደርን በገንዘብ ለመደገፍ የአውሮፓ ህብረት ባለው ቁርጠኝነት ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በተጨማሪም ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሮች የሚደረገውን ድጋፍ ለማጠናከር መግባባት መፈጠሩን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ፣ የኃይል ማስተላለፊያ እና ቀጣናዊ የኃይል ትስስር ፋይናንስን በማሳደግ አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ማፋጠን ላይ ትኩረት ያደርጋል።