AMN ጥር 20/2018
ሮተሪ ኢትዮጵያ በ70 ዓመታት የኢትዮጵያ ቆይታው በጤናው ዘርፍ ትርጉም ያለው ሥራ መስራቱን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ።mሮተሪ ኢትዮጵያ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመቱን በብሔራዊ ቤተ-መንግስት አክብሯል።
በዝግጅቱም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንትና የሮተሪ ኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሮተሪ ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንት ፍራንሲስኮ ኦሬዞ፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ሮተሪ ኢትዮጵያ ባለፉት 70 ዓመታት በጤና አገልግሎቶችና ሌሎች የልማት ዘርፎች ትርጉም ያለው ሥራ ሰርቷል። የጤና አገልግሎት ጥራትና ደረጃን ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራትም ፖሊዮን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።
ሮተሪ ኢትዮጵያ ልዩ እሴቶች እና ቁርጠኝነት ያለው ተቋም ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ የፖሊዮ በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦም አመስግነዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ ሮተሪ ኢትዮጵያ ፖሊዮን ከኢትዮጵያ በማጥፋትና በሌሎች የጤና ዘርፎች ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። በቀጣይም ከሮተሪ ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር የጤና ሥርዓቱን ለማሻሻል በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የሮተሪ ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንት ፍራንሲስኮ ኦሬዞ በበኩላቸው፤ ሮተሪ ኢንተርናሸናል በኢትዮጵያና ሌሎች ሀገራት ፖሊዮን የማጥፋት ዘመቻ ላይ በቢሊዮን ዶላር በላይ መድቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎትና ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ገንቢ ሚና ለመወጣት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩልም ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከሮተሪ ኢንተርናሽናል ፕሬዝዳንት ፍራንሲስኮ አሬዞን ጋር በጤና፣ በትምህርት፣ በሰላም ግንባታና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተወያይተዋል። በውይይቱም ሮተሪ ኢትዮጵያ የፖሊዮ በሽታን ከኢትዮጵያ በማጥፋት እና በሌሎች መስኮች ያከናወናቸው ተግባራት ገለፃ ተደርጓል።
በቀጣይም በኢትዮጵያ በጤና፣ በሰላም ግንባታና ተያያዥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች በትብብር መስራት የሚስችል የትኩረት አቅጣጫ መቀመጡን ኢዜአ ዘግቧል።
ሮተሪ ኢንተርናሽናል በዓለም ከ46 ሺህ በላይ ክለቦች ያሉት ሲሆን፤ በኢትዮጵያም በአዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ጎንደር፣ በጅማና በአዋሳ የሚገኙ ክለቦቹ በማህበረሰብ ተኮር ሥራዎች ላይ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል።