ሚዲያው በሁሉም አማራጮችአዳዲስ ይዘቶችን በመተግበርተደራሽነቱን የበለጠእንደሚያሰፋ ተገለጸ

You are currently viewing ሚዲያው በሁሉም አማራጮችአዳዲስ ይዘቶችን በመተግበርተደራሽነቱን የበለጠእንደሚያሰፋ ተገለጸ

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፣ ሚዲያው የህዝብ ጥያቄዎች የሚንሸራሸሩበት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችሉ መድረኮች መፍጠሩን ገልጸው፣ በቀጣይም በሁሉም አማራጮች አዳዲስ ይዘቶችን በመተግበር ተደራሽነቱን የበለጠ እንደሚያሰፋ ገልጸዋል።

ይህን የተባለው የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ውይይት በተካሄደበት ወቅት ነው፡፡ ሚዲያው በ2018 በጀት ዓመት በተለያዩ ዘርፎችና የስራ መስኮች በማከናወን ካቀዳቸው ተግባራት መካከል አብዛኞቹን በመፈጸም ከባለፈው ዓመት የላቀ አፈፃፀም ማስመዝገቡ በቀረበው ሪፖርት ተጠቅሷል።

በዚሁ መድረክ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ሚዲያው በይዘት በአቀራረብ፣ በቴክኖሎጂ እና በሰው ሀብት ልማት ግንባታ ለውጥ ማምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

አክለውም፣ ሚዲያው ባለፉት ጊዜያት የህዝብ ጥያቄዎች የሚንሸራሸሩበት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችሉ መድረኮችን መፍጠሩን ጠቁመው፣ ወደፊትም የአገልግሎት አሰጣጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ የሚያስችሉ አዳዲስ ይዘቶችን በመተግበር ተደራሽነቱን እንደሚያሰፋ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሠራተኛና አመራር ዋና ተልዕኮ በይዘት፣ በአቀራረብ፣ በሰው ኃይል አደረጃጃት እና በቴክኖሎጂ ግብዓት ተወዳዳሪና ተመራጭ መሆን ነው ያሉት አቶ ካሳሁን፣ የመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ መሆንን የማሳካት ግብ እውን ለማድረግ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች እጅ ለእጅ ተያይዘው በቁርጠኝነትና በትጋት እየሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የተቋሙ መለያ በሆኑት ዋርካ፣ አገልጋዩ እና በጠረጴዛ የተሰኙ ፕሮግራሞች በከተማዋ የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የህዝብ ዐይንና ጆሮ ሆኖ በትጋት እየሰራ እንደሆነ ጠቁመው፣ በቀጣይም ሰፊና ጥልቀት ያላቸው የምርመራ ዘገባዎችን በመስራት ተደራሽ ለመሆን እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

የምርመራ ስራ በዶክመንተሪ፣ በቶክ ሾውና በተለያየ መልኩ እንደሚሰራ ጠቁመው፣ አሁን ዋርካ፣ አገልጋዩና በጠረጴዛ እንደሚያቀርባቸው የምርመራ ሥራዎች ለወደፊቱ በዶክመንተሪ ለመስራት የሚያስችል ትልቅ አቅም መኖሩንም አመላክተዋል፡፡

የሚዲያ ስራ የአመራርና የሠራተኛውን ተነሳሽነትና ትጋት የሚጠይቅ ቢሆንም ይህን እውን ለማድረግ የሰው ሃይል ግብአት፣ በጀትና ሥራውን በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ለመስራት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ማሟላት የግድ በመሆኑ በዚህ ረገድ በትኩረት መሰራቱንም  ነው የተናገሩት፡፡

የከተማዋን ህዝብ የሚዲያ ጥማትና ፍላጎት ለማርካት ተቋሙ ከመቸውም በላይ የተሻለ ስራ በመስራት በገቢ ረግድም ከዓመት ዓመት ከፍተኛ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ሆኖም ግን ከተማዋ ካላት አቅም አኳያ አሁንም ቢሆን በተወሰነ መልኩ መሻሻል እንደሚገባው ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

የዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ፣ የአፍሪካውያን ዋና መቀመጫ፣ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የሆነችው ከተማችን በኢኮኖሚ፣በፖለቲካና በዲፕሎማሲው ረገድ እያመጣች ያለውን ለውጥ ሚዲያው እንደባለቤት መከተል ብቻ ሳይሆን አሁን ከሚሰራው በላይ ሰርቶ ማሳወቅ አለበትም ብለዋል፡፡

ብልሹ አሰራሮችን በማጋለጡ ረገድ በዋርካ፣ በአገልጋዩ፣ በጠረጴዛ የህዝብ ድምጽ የሚያሰኙንን ህዝብና መንግስትን የሚያገናኙ ስራዎች በተከታታይነት ተሰርተዋል ይላል ሪፖርቱ፡፡ እንደዚሁም ነዋሪው ችግሩን እና ጥያቄዉን በግልጽ ፊት ለፊት እንዲያነሳ እና ምላሽ እንዲሰጥብት፣ ብልሹ አሰራሮችም በህዝብ አስተያየት ተለይተው እንዲታረሙ የሚያስችሉ ሥራዎች ስለመሰራታቸው በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ በተጨማሪም የመንግስት አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት አገልግሎት በአግባቡ እየሰጡ ስለመሆኑ ክትትል እየተሰራ ስለመሆኑም እንደዚሁ ተገልጧል፡፡

የተቋማት አመራሮች  ችግሮችን ለመፍታት የገቡትን ቃል የት ደረሰ ብሎ በመጠይቅ፤ በተገባው ቃል መሰረት የተፈቱ ችግሮችን በተጠቃሚው አንደበት እንዴት እንደሚገለጽና፤ ላልተፈቱ ችግሮችም ለምን ብሎ በመጠየቅ አገልግሎትን የሚያሳልጥ ችግሮችን የሚፈታ ድንገተኛ ክትትል ማድረግም በሚዲያው ሲሰሩ መቆየቱን በዚህም ውጤት ስለመምጣቱ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

‎የትዉልድ ድምጽ የሆነዉ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ በመሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ከማገልገል አልፎ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት በመፈጸም የተሻለ ስራ ማከናወኑ በአፈጻጸም ሪፖርቱ ተነስቷል። ህዝብና መንግስትን ከማቀራረብ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ከማስቻል እና የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት እዉን እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ ሥራዎችን ማከናወኑን በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል።

ባለፉት ስድስት ወራት በከተማ አቀፍና በሀገር አቀፍ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ የሆኑ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተወዳዳሪ፣ተመራጭ እና እውነተኛ የሜትሮፖሊታን ሚዲያ መሆን የሚያስችለውን ስትራቴጂ በመከተል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ሚዲያው ባለፉት 6 ወራት በተለይ በቴክኖሎጂ አቅም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ማምጣቱን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ በቀጣይም በሁሉም አማራጮች አዳዲስ ይዘቶችን በመተግበር ተደራሽነቱን እንደሚያሰፋ ጠቅሰዋል፡፡

የተቋሙን የ6 ወራት አፈፃፀም በሪፖርት ያቀረቡት የስትራቴጂክ ሥራ አመራር ልማትና ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ አበበ ደሳለ፤ ሚዲያው ባለፉት 6 ወራት ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በከተማዋ የተከናወኑ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ለሕዝብ ይበልጥ እንዲተዋወቁ ተደርጓል ያሉት አቶ አበበ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት በቀጥታ ሥርጭት ለተመልካች ተደራሽ ሆነዋል ብለዋል።

ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተገናኘም በኑሮ ውድነት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በገቢ አሰባሰብ እና በከተማ ጽዳት ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ውጤት ተመዝግቧልም ብለዋል።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ፣ ሚዲያው ተወዳዳሪና ተመራጭ የሚያደርገውን አቀራረብ ወደ አድማጭ፣ ተመልካቾችና አንባቢያን እያደረሰ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

ሚዲያው የቋንቋዎች ቻናል በመክፈት ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን እንዲሁም የአድማጭ ተመልካቾቹን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለውን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ አውጥቶ በትጋት እየሰራ ነው፡፡

ተቋሙ በስትራቴጂክ እቅዱ ካስቀመጣቸው ዋና ዋና ሃሳቦች አንዱ ብዝሃነትን ማስተናገድ ሲሆን፣ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚኖሩባት ከተማ እንደመሆኗ ህዝቧን የሚመጥን የቋንቋ ብዝሃነትና የአቀራረብ ስብጥር እንዲኖር ታምኖበት የቋንቋዎች ቻናል ተከፍቶ የአፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛ፣ ትግረኛን ጨምሮ በሰባት የተለያዩ ቋንቋዎች ወደ ህዝብ እየደረሰ ይገኛል፡፡

መዲናዋ የብዝሃ ቋንቋ መገኛና የዲፕሎማቲክ ከተማ በመሆኗም ይህንን የሚመስል ሚዲያ መሆን ግድ ነበር፡፡ እንደዚሁም አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ከተማ እንደመሆኗ መጠን በተለያዩ የዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ላይም ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በተለያየ ዘርፍ በየጊዜው ለውጥ እያመጣ ሲሆን፣ ነገር ግን ገና ብዙ መስራት እንደሚጠይቅና ዋናው ግብም የበለጠ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ነው፡፡ ለዚህም ከሰው ኃይል በተጨማሪ ግብዓት የማደራጀትና የማሟላት ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

በመዲናዋ ላይ በፍጥነት እየመጣ ካለው ፈጣን ለውጥ ጋር እኩል መራመድና እየተከናወነ ያለውን ስራ ከስር ከስር መከተል ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በዓይነቱ ለየት ያለና በመዝናኛው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ የሚያመጣ “አዲስ ታለንት ሾው” የተሰኘ የኪነ ጥበብ ውድድር ሲያስተላፍ ቆይቶ ታህሳስ 29 ቀን 2018 ዓ.ም በሽልማት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

መረጃዎችን በፍጥነትና በጥራት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈም በመዝናኛው ዘርፍ አዝናኝና ትምህርት ሰጪ የሆኑ ፕሮግራሞችን ቀርጾ የ24 ሰዓት ስርጭት እየሰራም ይገኛል። ከዚህም ጎን ለጎን ሁሉም ፕሮግራሞች የየራሳቸው መለያ እንዲኖራቸው ጭምር ብራንዲንግ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በ2023 ዋና የሜትሮፖሊታን የከተማ ሚዲያ መሆን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያስቀመጠው ራዕይ ነው። ሚዲያው በኤ ኤም ኤን የቴሌቪዥን ቻናሎቹ፣ በኤፍ ኤም (FM 96.3) ሬዲዮ፣ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ፣ በዲጂታል ሚዲያ አማራጮች የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ በማስቻል፣ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶችን በማስተዋወቅ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና መጫወቱ ተጠቅሷል።

በትምህርትና ትውልድ ግንባታ፣ በሰላምና ጸጥታ እንዲሁም በከተማ ግብርና፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና የኑሮ ጫናን በማቃለል፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ፣ ቴክኖሎጂ እና መዝናኛ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ዜናዎችን፣ የቀጥታ ስርጭቶችን፣ ፕሮግራሞችንና ዘጋቢ ፊልሞችን ለተመልካች ያደርሳል፡፡

በሸዋርካብሽ ቦጋለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review