AMN- ጥር 26/2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን በ10ኛ መደበኛ ስብስባው የመንግስትን የ2018 የ6 ወራት የስራ አፈፃፃም እየገመገመ ይገኛል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም በሀገሪቱ ታሪክ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበበት ያለበት ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዋነኛ ዓላማ የሀገሪቱን የማክሮ ኢኮኖሚ የገጠሙትን ስንክሳሮችና ፈተናዎች ደረጃ በደረጃ መፍታት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ይህም የሀገሪቱን የፋይናንስ መዋቅር ጤናማ በማድረግ ለዘላቂ ዕድገት መሠረት ጥሏል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም ግብርና መር ዕድገት ብቻውን ሀገርን ከአረንቋ ሊያወጣ ስለማይችል፣ ብዝሃ-ዘርፍና ብዝሃ-ተዋንያን የሚሳተፉበት አቅጣጫ ተተልሟል ብለዋል።
የኢኮኖሚ ማሻሻያው በከተማም ሆነ በገጠር በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ላይ የሚታይና በትውልድ ላይ የሚፈጠረውን ጫና የሚቀንስ የኢኮኖሚ ስኬት እያመጣ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ላለፉት 20 ዓመታት ፕሮጀክት በሚል ሰበብ የተጠራቀመውና ለታለመለት ዓላማ ሳይውል የቀረው ጤነኛ ያልሆነ የብድር ሥርዓት ሀገሪቱን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከቷት ቆይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሪፎርሙ ይህን የእዳ ቀንበር በማቃለል ኢትዮጵያ የነበራትን ደካማ የብድር መክፈል ስም ለመቀየር በስኬት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የተመዘገበው የኢኮኖሚ እድገት በማንም መመዘኛ በማያከራክር ሁኔታ እያደገ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስተሩ፣ ይንንም የዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ አዝማሚያዎችን በስፋት ዳሰውና ተንትነው አስረድተዋል፡
ኢትዮጵያ ያከናወነችው የኢኮኖሚ ሪፎርም ዛሬ ባስገኘው ውጤት ብቻ ሳይሆን ነገ በምናልመው ታላቅ ኢኮኖሚ ሊመዘን ይገባል ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን