AMN- የካቲት 1/2018 ዓ.ም
በዚህም የአቃቂ ኢንተርናሽናል ስታዲየም እና የአቃቂ ድልድይ በዚህ ዓመት እንደሚጠናቀቁ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ተገኝተው የከተማ አስተዳደሩን የ6 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይህን የተናገሩት።
ከለውጡ በፊት በነበረው መንግስት ታቅዶ የነበረ እና በከተማው አቅም ቀርቶ በኢትዮጵያ አቅም አይቻልም ተብሎ የነበረውን የመንገድ ፕሮጀክት በከተማው በጀት መሥራት መቻሉን ከንቲባዋ ገልጸዋል።
ከለውጡ በፊት ኢትዮጵያ ብድር መውሰድ ከማይችሉ ሀገራት አንዷ ሆና እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ፣ በዚህ ምክንያት ለመሥራት ቃል ተገብተው የነበሩ መሠረተ ልማቶችም ባለመሠራታቸው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።
ጥያቄው በከተማው ምክር ቤት ጭምር ሲነሳ የነበረና ከ2014 ዓ.ም በኋላ በከተማ በጀት ከ23 ኪሎ ሜትር በላይ አቃቂ ቱሉዲምቱ፣ አቃቂ ቃሊቲ እና በቦሌ ቡልቡላ በኩል ወደ ካርጎ የሚገጥመው መንገድ መሠራቱን ተናግረዋል።
ይህም በምክር ቤቱ በጀት ጸድቆ በተያዘ ፕሮጀክት ነው ረጃጅም እና ሰፋፊ የሚባሉ የመጀመሪያዎቹ ትላልቅ ድልድዮች በከተማዋ የተሰሩት ብለዋል።
አዲስ አበባ ጀምራ የማትጨርሳቸው ፕሮጀክቶች የሉም በማለት ያረጋገጡት ከንቲባዋ፣ ድልድዩም በተመሳሳይም የአቃቂ ኢንተርናሽናል ስታዲየምም በዚህ ዓመት ለመጨረስ የተያዙ ፕሮጀክቶች ናቸው በማለት አረጋግጠዋል።
በታምራት ቢሻው