AMN – የካቲት 7/2018 ዓ.ም.
በጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ቋሚ መቀመጫ አለማግኘት ማስተባበያ የሚቀርብለት ጉዳይ አይደለም በማለት የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሕብረቱ አዳራሽ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
አለመተማመን እና መከፋፈል በሰፈነበት ዓለም የአፍሪካ ሕብረት ለባለብዙ ወገን ትበብር ምሳሌ መሆኑን የገለጹት ዋና ጸሐፊው ስለአፍሪካ ፍትሕ እና ዕኩልነት በተለያዩ ሁኔታዎች እና ቦታዎች ድምጻቸውን ማሰማታቸውን አሳውቀዋል።
አንቶኒዮ ጉተሬዝ በርካታ አሰርት ዓመታትን የተሻገረው የሕብረቱ እና የተባበሩት መንግስት ድርጅት ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ መሻገሩንም ተናግረዋል።
ተመድ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በሰላምና ጸጥታ፣ በዘላቂ ልማት እና በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዙሪያ በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል ዋና ጸሐፊው።
“አፍሪካ በጠረጴዛው ዙሪያ መኖር አለባት” ያሉት ዋና ጸሐፊው የአሕጉሪቱ ድምጽ እንዲሰማ እና በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንድታገኝ ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።
ከአፍሪካ ጋር በሶስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ያሉት ዋና ጸሐፊው የአሕጉሪቱ ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ የኃይል ዘርፍ እንዲያድግ በትብብር እንሠራለን ያሉት ጉቴሬዝ አፍሪካውን ከማዕድን ሀብታቸው ተጠቃሚ መሆን ስላለባቸው ከዚህ በላይ ብዝበዛ ይብቃልም ብለዋል።
በአሰግድ ኪዳነማርያም