የማታንቀላፋ መዲና

You are currently viewing የማታንቀላፋ መዲና

“ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን አብዝቶ የሚያስተናግድ ሀገር፣ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መድረክ ተሰሚነቱ ይጨምራል”

                                                                                                  የምጣኔ ሀብት መምህር ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)

ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የሩዋንዳዋ ዋና ከተማ ኪጋሊ ማታ ላይ ጭልጭል የሚሉ መብራቶች ብቻ የሚታዩባት፣ የፀጥታ ስጋት የነበረባትና እንቅስቃሴ የተገታባት ከተማ ነበረች። መሪዎቿ ግን ‘ባለ 24 ሰዓት ከተማ’ (24-Hour City) የመሆን ራዕይ ሰነቁ። ከተማዋን በዘመናዊ የጎዳና መብራቶች አጥለቅልቀው አስፈላጊውን መሰረተ ልማት ሲያሟሉላት የምሽት የንግድ ስራዋ መሟሟቅ ጀመረ፤ እርምጃው በዓለም አቀፍ ደረጃ ኪጋሊን በደህንነቷ ቀዳሚ አደረጋት፤ የከተማዋ ነዋሪዎችና እንግዶች እኩለ ሌሊት ላይ በእግር እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ‘የመተማመን ስነ-ልቦና’ አላበሳት።

ኪጋሊ የምሽት አገልግሎቷን በማራዘሟ ያገኘችው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ነው። የምሽት አገልግሎት መጀመሩ በቀን የሚሰሩት እንደተጠበቁ ሆነው፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በምሽቱ ክፍለ ጊዜ በሆቴሎች፣ በፋርማሲዎች፣ በትራንስፖርት እና በሱቆች እንዲቀጠሩ አድርጓል።

የ‘ኪጋሊ የ2050 መሪ ፕላን’ (Kigali Master Plan 2050) ሰነድ ላይ እንደተብራራው፣ ነጋዴዎች ቀደም ብለው ሱቆቻቸውን እስከ ምሽቱ 6 እና 7 ሰዓት ድረስ ሳይዘጉ በማቆየታቸው የሽያጭ መጠናቸውን ከ20 በመቶ እስከ 30 በመቶ ድረስ አሳድገዋል። በቀን ብቻ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ መንገዶችና ህንጻዎች፣ በሌሊትም ጭምር አገልግሎት በመስጠታቸው ለከተማዋ የንግድና የኢንቨስትመንት ስራ መስፋፋት ምክንያት ሆነዋል።

ዛሬ ላይ ኪጋሊ በአፍሪካ የ‘ማይስ ቱሪዝም’ (MICE፡- Meetings, Incentives, Conferences, and Exhibitions) ማዕከል ከሆኑ ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ሆናለች። ይህ ስኬት ከምሽት የንግድ እንቅስቃሴዋ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሲሆን፣ አንድ የዓለም አቀፍ ስብሰባ ተሳታፊ ቀኑን ሙሉ አዳራሽ ውስጥ ውሎ ሲወጣ፣ ምሽት ላይ የሚዝናናበት፣ የሚገበያይበትና የከተማዋን ባህል የሚቃኝበት አማራጭ ያገኛል። ይህ እንግዶች በከተማዋ የሚቆዩበትን ቀን ያረዝመዋል።

አዲስ አበባም የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የጎዳና ላይ መብራቶችንና ሰፋፊ የእግር መንገድ አማራጮችን በማዘጋጀት፣ ይህንን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ በተግባር እያዋለችው ትገኛለች። አዲስ አበባ ለረጅም ዘመናት ‘ቀን ሰርቶ ማታ የሚተኛባት’ ከተማ ሆና ቆይታለች። ፀሐይ ስትጠልቅ የንግድ ሱቆች በር መዝጊያ ድምፆች ይሰማሉ፤ የከተማዋ እንቅስቃሴም አብሮ ይረግባል። ሆኖም በቅርቡ የተጀመረው የምሽት ንግድና አገልግሎት እንቅስቃሴ ይህንን የታሪክ ምዕራፍ እየቀየረው ነው። ከተማዋ በኮሪደር ልማትና በዘመናዊ መሰረተ ልማቶች ከተዋበች በኋላ፣ ምሽቱ ለተጨማሪ ግብይት፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለከተማዋ ህያውነት አዲስ በር ከፍቷል።

ይህን ሀቅ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው ነጋዴዎችም ይመሰክራሉ፡፡

የአፍሪካ ህብረት እና የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባ በየሳምንቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ እንግዶችን ታስተናግዳለች። ከዚህ ቀደም ስብሰባ ያጠናቀቁ ተሳታፊዎች ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ የሚንቀሳቀሱባቸው እና የሚገበያዩባቸው ቦታዎች ውስን ነበሩ። አሁን ግን አንድ ዲፕሎማት ወይም የ‘ቢዝነስ’ እንግዳ ቀን ስብሰባውን አጠናቅቆ፣ ምሽት ላይ በነፃነት ወጥቶ የኢትዮጵያን ባህላዊ ምርቶች፣ አልባሳት እና ቅርሳቅርስ መገበያየት እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል። ለዚህም የዝግጅት ክፍላችን ተዘዋውሮ የተመለከታቸው የሽሮ ሜዳ፣ ሳር ቤት፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ እና መሰል አካባቢዎችን በእማኝነት መጥቀስ በቂ ነው።

አዲስ አበባ ዛሬ ከእንቅልፏ ነቅታለች፤ በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት የከተማዋ የደም ሥሮች የታደሱ ይመስላሉ። በሌሊት ብርሃን የሚደምቁ አዳዲስ አስፋልቶች፣ እንደ መስታወት የሚያብረቀርቁ የእግረኛ መንገዶችና ያለገደብ የሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎች ከተማዋን “የምስራቅ አፍሪካ ዱባይ እያደረጓት ነው” የሚሉ አስተያየቶችም ተዘውትረው ይሰነዘራሉ፡፡

አሁን አዲስ አበባ በርካታ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ አቅም ፈጥራለች፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ለከተማዋ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ባቀረቡት የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያው 6 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከተማዋ ከ150 በላይ ታላላቅ ኮንፈረንሶችን ማስተናገዷን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ስብሰባ ያጠናቀቁ እንግዶች በትራንስፖርት ብቻ ይንቀሳቀሱባቸው የነበሩ አካባቢዎች በእግር መጓዝ የሚያስችል ሰፊና ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ ተዘርግቶላቸዋል። ኤድና ሞል እና በአካባቢው ያሉ የገበያ ማዕከላት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ክፍት በመሆናቸው፣ ዲፕሎማቶች እና ቱሪስቶች በነፃነት እየተገበያዩ ይገኛሉ። ሳርቤትና ካዛንቺስን የመሳሰሉ አካባቢዎች የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ እንደመሆናቸው፣ ካፌዎቻቸውና ሱፐር ማርኬቶቻቸው 24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን በቅኝታችን ወቅት አረጋግጠናል።

ድሮ ፒያሳ ማታ ላይ ጭልጭል የምትልና እንቅስቃሴ የሚገታባት ነበረች። ዛሬ ግን በአዳዲስ መብራቶች ደምቃለች። ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ የሚያቀናው መንገድ ለምሽት የእግር ጉዞና ለግብይት ምቹ ሆኗል። አነስተኛ ነጋዴዎችና የቅርስ መሸጫዎች የሥራ ሰዓታቸውን አራዝመዋል፤ ይህም ‘ፒያሳ አትተኛም’ የሚለውን አባባል በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የስብሰባ ተሳታፊዎች ከስብሰባ በኋላ በቅርብ ርቀት ወጥተው የሚፈልጉትን ዕቃ መሸመት የሚችሉባቸው ‘ሚኒ ሞሎች’ በስፋት እየተከፈቱ ነው። በኮሪደር ልማቱ የተተከሉ አበባዎች፣ ውብ የፏፏቴዎች እና የጥበብ ስራዎች ለገዥውም ሆነ ለሻጩ አዎንታዊ ስነ-ልቦና ፈጥረዋል። በሌላ በኩል ከተማዋ 24 ሰዓት በብርሃን መጥለቅለቋ ነዋሪው ያለ ምንም ስጋት ንብረቱን ይዞ እንዲንቀሳቀስና ግብይት እንዲፈፅም አድርጎታል።

እንደ ቦሌ እና ሲ.ኤም.ሲ አካባቢዎች በሞሎቻቸውና በዘመናዊ መገበያያ ማዕከሎቻቸው ቀድሞውኑ የምሽት እንቅስቃሴ የነበረባቸው ቢሆንም፣ አሁን ግን የኮሪደር ልማቱ ተጨምሮበት ይበልጥ ደምቀዋል። ሜክሲኮና ሳርቤት ደግሞ በዘመናዊ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች ልዩ ድምቀትና ድባብ ተላብሰዋል። በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ለንግድ ምቹ የተደረጉ ሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠራቸው፣ ነጋዴዎች እስከ ምሽቱ 5 እና 6 ሰዓት ድረስ ምርቶቻቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥቷቸዋል።

እንደ ኤድና ሞል፣ ደምበል፣ ሴንቸሪ ሞልና ሌሎች ታላላቅ የንግድ ማዕከላት የአገልግሎት ሰዓታቸውን ማራዘማቸው ለመዲናዋ ነዋሪዎችም ቢሆን ትልቅ እፎይታ ሰጥተዋል። ቤተሰቦች ከስራ በኋላ ተገናኝተው የሚገበዩበት፣ ህፃናት የሚጫወቱበትና እራት የሚበሉበት ‘የምሽት ባህል’ እየተገነባ ነው። ይህ ደግሞ ለነጋዴዎች የሽያጭ መጠን ስለመጨመሩና ተጨማሪ ሰራተኞችን ለመቅጠር ዕድል መፍጠሩን በአካባቢው ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው የንግዱ ማህበረሰብ አባላት አረጋግጠውልናል፡፡

‘ዘ ክሬኤቲቭ ሲቲ’ (The Creative City) የተሰኘ መጽሐፍ ደራሲና ታዋቂ የከተማ ልማት ባለሙያ ቻርልስ ላንድሪ “አንዲት ከተማ 24 ሰዓት ክፍት መሆኗ ከኢኮኖሚው ባለፈ ማህበራዊ ደህንነትን ያረጋግጣል” ይላሉ። ሰፋፊ የእግር መንገዶችና የጎዳና መብራቶች ‘ተፈጥሯዊ ክትትልን’ (Natural Surveillance) እንደሚፈጥርና ብዙ ሰው በጎዳናዎች ላይ በቆዩ ቁጥር ወንጀል የመፈጸም ዕድሉ ይቀንሳል ባይ ናቸው ቻርልስ ላንድሪ።

አዲስ አበባ ከዚህ አንጻር ስትመዘን አሁን ላይ ‘የከተማ ስነ-ልቦናዋ’ የተቀየረ ሲሆን፣ ይህም ለምሽት ንግድ ትልቅ ዋስትና ሆኗል፡፡ የከተማ ልማት ባለሙያው ቻርልስ ላንድሪ፣ የምሽት ንግድ ከተሞችን ሕያው የሚያደርግ፣ ለነዋሪዎች ተጨማሪ የሥራ እድል እና የመዝናኛ አማራጭ የሚፈጥር መሆኑን ይገልጻሉ።

አዲስ አበባ ቀን ብቻ ሳይሆን ማታም የምትሰራ ከተማ መሆኗ ለኢኮኖሚ እድገቷ ወሳኝ ምዕራፍ ስለመሆኑ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር) ይናገራሉ። የምሽት ግብይት መስፋፋት የከተማዋን የኑሮ ዘይቤ ከማዘመኑ ባለፈ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የንግድ እንቅስቃሴውን በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፣ ዛሬ በአራቱም አቅጣጫዎች የሚታየው ብርሃንና እንቅስቃሴ፣ አዲስ አበባ ወደ ዓለም አቀፍ የንግድ ከተማነት እየተሸጋገረች መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ብለዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት የምሽት ኢኮኖሚ ማለት ‘የሀብት ብክነትን ማስቀረት ማለት ነው። በቀን ብቻ አገልግሎት የሚሰጡ መንገዶች፣ ህንጻዎችና መብራቶች ማታም ስራ ላይ ሲውሉ የሀገሪቱን የካፒታል አጠቃቀም ውጤታማ ያደርጉታል። የሽያጭ ሰዓት ከ8 ሰዓት ወደ 16 ወይም 24 ሰዓት ሲያድግ፣ የንግድ ድርጅቶች የምርት ሽግግር (Turnover) ይጨምራል። ይህ ደግሞ ለወጣቶች ‘የምሽት ፈረቃ’ (Night Shift) የስራ እድል በመፍጠር የስራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍ ትልቅ አቅም አለው ይላሉ፡፡

ከዓለም አቀፍ ስብሰባዎች አንጻር ከታየም አንድ እንግዳ በቀን ስብሰባ ውሎ ማታ ሆቴል ውስጥ ብቻ መታጠር የለበትም። ማታ ወጥቶ መገበያየቱ፣ የከተማዋን ውበት ማየቱና የባህል ምግቦችን መመገቡ በከተማዋ የሚኖረውን ቆይታ ያራዝመዋል። ይህም ሲሆን የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮች እንደሚሰፉና የንግድና የገበያ ግንኙነቶችን ለመፍጠር፣ ውል ለመፈራረም፣ ሽያጭና ግዢ ለመጀመር መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራሉ ይላሉ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ጉቱ ቴሶ (ዶ/ር)። ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ዝግጅቶችን አብዝቶ የሚያስተናግድ ሀገር፣ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መድረክ ተሰሚነቱ ይጨምራልም ይላሉ።

ዩኤን ሀቢታት ይፋ ያደረገው መረጃ አንድ የዓለም አቀፍ ስብሰባ ተሳታፊ በአንድ ከተማ ውስጥ ደህንነቱ ተጠብቆ የምሽት እንቅስቃሴ ካደረገ፣ በከተማዋ የሚያወጣው ገንዘብ በቀን ብቻ ከሚንቀሳቀስ ተጓዥ እንደሚበልጥ ያብራራል። በኮሪደር ልማት ውስጥ የሚካተቱ ሰፋፊ የእግር መንገዶች እና የብስክሌት መስመሮች የምሽት ቱሪዝምን ከፍ ያደርጋሉ።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review