የአንድነት መዝሙር – የነፃነት ዜማ

You are currently viewing የአንድነት መዝሙር – የነፃነት ዜማ

ብሔራዊ መዝሙር (Anthem) የአንድ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ማንነት፣ ታሪክ፣ እምነትና ተስፋ በዜማና በግጥም የሚገለጽበት ዓርማ ነው። ልክ እንደ ሰንደቅ ዓላማ ሁሉ፣ ብሔራዊ መዝሙር የሀገር ሉዓላዊነትና የአንድነት መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

በአንድ ሀገር ወይም አህጉር ውስጥ የተለያዩ ማኅበረሰቦች፣ ቋንቋዎችና እምነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ብሔራዊ መዝሙር ግን እነዚህን ልዩነቶች አሰናኝቶ “እኛ” የሚል የወል ማንነት ይፈጥራል። ዜጎች መዝሙሩን በአንድ ላይ ሲዘምሩ፣ የግል ማንነታቸውን ወደ ጎን ትተው ለሀገራዊ ወይም አህጉራዊ ማንነታቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ ያደርጋቸዋል። ይህ ድምፅ የወል ማንነት መገለጫም ነው። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም ይህንን መነሻ በማድረግ የአፍሪካ ሕብረት መዝሙርና በውስጡ የያዛቸው አንኳር መልዕክቶች ላይ አጭር ዳሰሳ አድርጓል።

የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር እንደ የወል ዜማ

ብሔራዊ መዝሙር ለአንድ ሀገር የሉዓላዊነት ምልክት፣ የታሪክ ማኅደር እና የሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ እንደሆነ ሁሉ፣ አህጉራዊ መዝሙርም የሚሊዮኖች ድምፅና የጋራ ዕጣ ፈንታ መግለጫ ነው። የታሪክና የተጋድሎ ማስታወሻ ተደርጎ የሚወሰደው የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር “Let Us All Unite and Celebrate Together” (ሁላችንም በአንድነት እንዘምርና እናክብር) በሚል መሪ ሐሳብ ይታወቃል።

የመዝሙሩ ግጥምና ዜማ የአህጉሪቱን ያለፈ ታሪክ በጥልቀት ይዘክራል። አፍሪካ የሰው ልጅ መገኛ ከመሆኗም በላይ፣ ለዘመናት የቅኝ አገዛዝን መራር ጽዋ የቀመሰች አህጉር ናት። መዝሙሩ ይህንን ያለፈውን ዘመን በማስታወስ፣ አፍሪካውያን በጋራ ታግለው ያገኙትን ነፃነት በኩራት እንዲያወሱ ያደርጋል።

የመዝሙሩ ስንኞች የአፍሪካን ልጆች ተጋድሎና ለነፃነት የተከፈለውን መሥዋዕትነት ይዘክራሉ። ይህም ለአዲሱ ትውልድ ነፃነት በዋጋ የተገኘ መሆኑንና ይህንን ነፃነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ያስገነዝባል። ታሪክን መዘከር ብቻ ሳይሆን፣ ካለፈው ቁስል ተፈውሶ ለአዲስ ጉዞ መነሳሳትን የሚሰብክ የድል አዋጅ ነው – የሕብረቱ መዝሙር።

ሌላው የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር ካለፈው ታሪክ ይነሳና ስለ ወደፊቱ ብሩህ ተስፋ ያመለክታል። የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ የፖለቲካ አንድነትና የሕዝቦችን ብልፅግና እንደ ትልቅ ራዕይ ያስቀምጣል። “አፍሪካን የሰላም እና የብልጽግና ምድር እናድርጋት” የሚለው መልዕክት ዜጎች ለሀገራቸው ብቻ ሳይሆን ለአህጉራቸው ዕድገት እንዲተጉ ያነሳሳል።

የጋራ ታሪክና ነጻነት ሲዘከር

የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር የተጻፈው በኢትዮጵያዊው ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ነው። ሙዚቃውን ያቀናበረው ደግሞ ኬንያዊው አርተር ሙዶጎ ከሞሊ ነው። የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር ለአፍሪካ አህጉር የታሪክ፣ የአንድነት፣ የተስፋ እና የእድገት ምልክት ሆኗል። ሁለቱ አፍሪካውያን ከያኒዎች የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር የአፍሪካውያንን ሕብረት የሚያበረታታ፣ አንድነት፣ ኩራት እና ብሩህ ተስፋን የሚፈጥር መዝሙር ለመሥራት ጥረት አድርገዋል።

ከሕብረቱ የመዝሙር ስንኞች እየመዘዝን የመዝሙሩን አንኳር መልዕክቶች አብረን እንመልከት፦

“Let us all unite and celebrate together

The victories won for our liberation

Let us dedicate ourselves to rise together

 To defend our liberty and unity…” ይህ ግጥም መልዕክቱ ወደ አማርኛ ሲመለስ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

     (በአሸናፊነታችን ነጻነታችንን ተጎናጽፈናል

     ሁላችንም ተባብረን በጋራ ነጻነታችንን

እናክብር

 በጋራ ለማደግ በቁርጠኝነት እንጠንክር

ነፃነታችንን እና አንድነታችንን  ለማስጠበቅ እንተባበር… ።)

ከላይ የሰፈሩት ስንኞች ከሕብረቱ መዝሙር ውስጥ የተወሰዱ ናቸው። ስንኞቹ በውስጣቸው ጥልቅ መልዕክት ይዘዋል። ለአብነትም “በአሸናፊነታችን ነጻነታችንን ተጎናጽፈናል”(The victories won for our liberation) የሚለው ስንኝ፣ የአፍሪካን ያለፈ ታሪክ የሚዘክር ነው። ነፃነት በስጦታ የተገኘ ሳይሆን በታላቅ አሸናፊነት እና ተጋድሎ የመጣ መሆኑን አጽንኦት ይሰጣል። አፍሪካውያን የቅኝ ግዛትን ቀንበር የሰበሩት በጀግንነት መሆኑን በመግለጽ፣ በትውልዱ ውስጥ የበታችነት ስሜት እንዳይኖር በማድረግ በኩራት እንዲሞሉ ያደርጋል።

የመዝሙሩ መግቢያ ላይ “ሁላችንም ተባብረን በጋራ ነጻነታችንን እናክብር”(let us all unite and celebrate together) ይላል። ይህ ትኩረቱን ያደረገው “አንድነት” ላይ ነው። ነፃነትን ብቻውን ማክበር አይቻልም፤ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው መላው አህጉር በአንድነት ሲቆም ነው።“celebrate” (ማክበር) የሚለው ቃል ነፃነትን እንደ ትልቅ ስኬት እንድንመለከተው ያደርጋል፡፡

“በጋራ ለማደግ በቁርጠኝነት እንጠንክር” (Let us dedicate ourselves to rise together) የሚለው ስንኝ ደግሞ፣ ከፖለቲካዊ ነፃነት ባለፈ ወደ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ያተኩራል። “Rise” (መነሳት/ማደግ) የሚለው ቃል አፍሪካ ካለችበት የድኅነት አዙሪት ወጥታ ወደ ከፍታ የመውጣት ራዕይን ያሳያል። ይህም ዕድገት በምኞት ብቻ ሳይሆን በ“ቁርጠኝነት” የሚመጣ፣ ዕድገቱም ግለሰባዊ ሳይሆን የጋራ መሆን እንዳለበት ያስገነዝባል።

“ነፃነታችንን እና አንድነታችንን ለማስጠበቅ እንተባበር” (To defend our liberty and unity) የሚለው ስንኝ መከላከያ ወይም ጥበቃ ላይ ያተኩራል። ነፃነትን ማግኘት አንድ ነገር ሲሆን፣ አስጠብቆ መቆየት ደግሞ ሌላ ትልቅ ስራ ነው። አፍሪካውያን ያገኙትን ነፃነትና አንድነት የሚቀሙ የውስጥና የውጭ አደጋዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን አደጋዎች ለመከላከል ደግሞ ብቸኛው መሣሪያ መተባበር መሆኑን ይገልጻል።

አፍሪካን እንደ ሕይወት ዛፍ

የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር ውስጥ ታሪክን ብቻ ሳይሆን አፍሪካ በውስጧ የያዘቻቸውን እንቁዎች ጭምር ያወሳል። አፍሪካን “በሕይወት ዛፍነት” ይመስላታል። ለአብነትም የሚከተሉትን ስንኞች እንመልከት፦

“O Sons and Daughters of Africa

 Flesh of the Sun and Flesh of the Sky

 Let us make Africa the Tree of life

 Let us all unite and sing together

 To uphold the bonds that frames our destiny

 Let us dedicate ourselves to fight together

 For lasting peace and justice on the earth…”

 (የአፍሪካ ልጆች ሆይ

 የጸሐይና የሰማይ ቀለማት

 አፍሪካን የሕይወት ዛፍ እናድርጋት

 ሁላችንም ተባብረን በጋራ እንዘምር

ዕጣ ፈንታችንን የሚያጎናጽፉንን ማሰሪያዎች እናጠንክር

 በጋራ ለመታገል ራሳችንን እናዘጋጅ

በምድር ላይ ዘላቂ ሰላምና ፍትሕ እንዲኖር…።)

ከላይ የሰፈሩት የግጥም ስንኞች አፍሪካ የወጣቶች መገኛ ምድር እንደመሆኗ፣ ለኑሮ ምቹ፣ ውብ፣ ማራኪና የሰከነ ህይወት የሚኖርባት ምድር እናድርጋት ይላል። ስንኞቹ መዝሙሩን ከታሪክና ከፖለቲካዊ ገጽታው ባሻገር ወደ መንፈሳዊ እና ተፈጥሯዊ ትስስር ከፍ ያደርጉታል። “የፀሐይና የሰማይ ቀለማት” (Flesh of the Sun and Flesh of the Sky) የሚለው አገላለጽ አፍሪካውያን ከተፈጥሮ ጋር ያላቸውን ጥልቅ ቁርኝትና የከበረ ማንነት ይገልጻል። አፍሪካን እንደ “ህይወት ዛፍ” (Tree of Life) የመመሰል ርዕይ ደግሞ አህጉሪቱ ለልጆቿ መጠለያና መረጋጋትን የምትሰጥ ምድር እንድትሆን የሚያልም ነው።

“እጣ ፈንታችንን የሚያጎናጽፉንን ማሰሪያዎች እናጠንክር” (To uphold the bonds that frame our destiny) የሚለው ስንኝ በውስጡ ጥልቅ መልዕክት ይዟል። ስንኙ ውስጥ “ማሰሪያዎች” (Bonds) ተብለው የተገለጹት የአፍሪካውያን የጋራ እሴቶች፣ ባህሎችና የታሪክ ትስስሮች ናቸው። ይህም አፍሪካውያንን የሚያስተሳስራቸው ነገር ከሚለያያቸው ነገር እንደሚበልጥ ይነግረናል። የጋራ እጣ ፈንታችን (Destiny) የተገነባው በእነዚህ ማሰሪያዎች ላይ በመሆኑ፣ እነሱን መጠበቅና ማጠናከር የህልውና ጉዳይ መሆኑን የግጥሙ ስንኝ ያስገነዝባል።

በአጠቃላይ፣ የአፍሪካ ህብረት መዝሙር የአህጉሪቱ የነፃነት፣ የአንድነትና የተስፋ ምልክት ነው። ያለፈውን ታሪክ በማስታወስ፣ የአሁኑን ማንነት በማረጋገጥና የወደፊቱን ብሩህ መንገድ በመጠቆም ረገድ የሚጫወተው ሚና የማይተካ ነው። መዝሙሩ የድምፅና የዜማ ስብስብ ብቻ ሳይሆን፣ የአፍሪካውያን የጋራ የልብ ዜማ ነው ሊባል ይችላል።

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review