AMN- የካቲት 11/2018 ዓ.ም
ለሰዲ ጫንቃ እና ሃዋ ገላን ወረዳዎች ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ ያለውን የቄጦ የመስኖ መሠረተ ልማት ፕሮጀክትን ለመመልከት እድል አግኝቻለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ፕሮጀክቱ ለግብርና ሥራ የማይቋረጥ የውሃ አቅርቦትን በሚያረጋግጥ መልኩ የአካባቢውን የተፈጥሮ መልክዓ-ምድር በአግባቡ ለመጠቀም ታስቦበት የተተገበረ ነው ብለዋል።

የመስኖ ሥራውን በቀጥታ ጥቅም ላይ በማዋል የታረሰ እና የለማ መሬት ለኅብረተሰቡ ጉልህ ፋይዳ ማስገኘት መጀመሩም አበረታች ነው።
አብሮ የተሠራው የመንገድ መሠረተ ልማትም የገበያ ተደራሽነትን አስፍቷል፣ የነዋሪዎችን የቀን ተቀን ኑሮ እንቅስቃሴንም አቅልሏል ብለዋል።

አካባቢው ሰፊ የግብርና እምቅ አቅም ያለው እንደመሆኑ እንደ ስንዴ፣ ሩዝ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ እና ብርቱካን ያሉትን ምርቶች በመደገፍ ረገድ የመስኖ እና የመሠረተ ልማት ሥራ ዘላቂ የገጠር ግብርና ልማትን ማሳደግ እንደሚችሉ አብነት ነው በማለትም አክለዋል።