የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታና የትራንስፖርት ፍሰትን አዘምኗል

You are currently viewing የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታና የትራንስፖርት ፍሰትን አዘምኗል

AMN- የካቲት 13/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ ይፈጠር የነበረውን እንግልት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያመጣ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በተለይም በሽሮ ሜዳ እና በአራት ኪሎ አካባቢ የታዩት የልማት ለውጦች የከተማዋን የትራንስፖርት መሠረተ ልማት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው።

ቀደም ሲል በከተማዋ ይታይ የነበረው የመንገድ መጥበብ እና የትራፊክ መሳከር በነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ እንግልት ይፈጥር እንደነበርም አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች እየተገነቡ እንደሚገኙ የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፤ በተለይም የአራት ኪሎ መንገድ ወደ አንድ አቅጣጫ ሦስት፣ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሦስት በድምሩ ባለ ስድስት መስመር (6 Lane) ሆኖ መገንባቱ የትራፊክ ፍሰቱን ያሳለጠና የትራንስፖርት ሥርዓቱን ያዘመነ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የግንባታ ስኬትም ለከተማዋ ዕድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ እግረኞች ከመኪና ጋር ተቀላቅለው የሚጓዙባቸውና ለቆሻሻ የተጋለጡ መንገዶች ይበዙ እንደነበር ነዋሪዎቹ አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት ሰፊና ደረጃቸውን የጠበቁ የእግረኛ መንገዶች በመገንባታቸው ያለምንም ስጋትና እንግልት የመንቀሳቀስ ነፃነት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በተለይ በሽሮ ሜዳ አካባቢ የታዩት የልማት ሥራዎች የመንግሥትና የነዋሪዎች ትብብር ውጤት መሆናቸውን ነዋሪዎች ጠቅሰው፤ ለልማቱ ያሳዩት ድጋፍና ትዕግሥት ለሥራው ስኬታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማቱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለጎብኚዎች ደግሞ ሳቢ የማድረግ ዓላማውን በውጤታማነት እያሳካ እንደሚገኝ በግንባታዎቹ ላይ የታዩ ለውጦች ምስክር መሆናቸው ተመላክቷል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review