ልዩነታቸው በጋራ ከመቆምና ነጭ ወራሪዎችን ከማንበርከክ ያልገታቸው አይበገሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን

You are currently viewing ልዩነታቸው በጋራ ከመቆምና ነጭ ወራሪዎችን ከማንበርከክ ያልገታቸው አይበገሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን

AMN የካቲት 14/2018 ዓ.ም

በነጭ ወራሪዎች ባለመገዛት ታሪኳ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ የሚነገርላት ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች መገኛ ነች፡፡

እነዚህ ብሔሮች ፤ ብሔረሰቦች የየራሳቸዉ ሃይማኖት፤ ቋንቋ፤ ባህል፤ ታሪክ ፤ ማንነትና ባህላዊ እሴት ያላቸዉ ህዝቦች ናቸዉ፡፡

ሁሉም የሚግባቡበት አንድ የጋራ ሃገር – ኢትዮጵያ፡፡

የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል የሆኑት ኢትዮጵያዊያን ነጭ ወራሪ ሃይል ባህርና ድንበር ተሻግሮ ሐገራቸውን ሊወር ሲመጣ ብሔራቸዉ፤ ሃይማኖታቸዉ፤ ቋንቋቸዉ፤ ጾታቸዉ፤ ባህላቸዉ እና ማንነታቸዉ ልዩነት እንዳልፈጠሩባቸዉ ፤ ይልቁንም አንድነትና ህብረታቸዉን ይበልጥ እንዳጸኑላቸዉ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡

የደቡብ አፍሪካዉ የነጻነት ታጋይ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ “የ1896ቱ (እ.ኤ.አ) የዓድዋ ድል የአፍሪካን ሕዝቦች አይበገሬነት ያሳየ እና በወቅቱም በመላ አህጉሪቱ ከቅኝ አገዛዝ ጋር ሲዋጉ ለነበሩት ሁሉ አነሳሽ ሆኗል” ሲል ገልጸዋል፡፡

“የዓድዋ ጦርነት በአፍሪካ ታሪክ ድርሳን አፍሪካዊያን ተባብረዉ የቅኝ ገዢ ኃይሎችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያመላከተ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነበር” ሲሉ የታሪክ አሻራቸዉን ያኖሩት ደግሞ የፓንአፍሪቃ አቀንቃኝ የነበሩት ጋናዊዉ ክዋሜ ንክሩማህ ናቸው፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተን ቸርችል በበኩላቸዉ “ኢጣሊያ በኢትዮጵያዊያን የደረሰባት አስከፊ ሽንፈት በአዉሮፓዊያን ኩራት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል” ሲሉ ስለ አድዋ ጀግኖች ቆራጥነትና አይበገሬነት መስክረዋል፡፡

ዘመን የማይሽረዉ የአድዋ ጀግኖች ታሪክ በትላንትናዎቹ መሪዎችና ትዉልድ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ እና በዓለም መሪዎች አልፎም በአዲሱ ትዉልድ በታላቅ ድል እና ክብር እየተዘከረ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መሃል ፒያሳ ላይ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ደግሞ የዓድዋ ጀግኖች ያለምንም የብሔር፤ የሃይማኖት፤ የቋንቋ እና ጾታ ልዩነት በጋራ እና በአንድነት እንዲዘከሩ መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ዐድዋ የአፍሪካ ድል ነዉ::አፍሪካዊያን ቅኝ ግዛትን ፈጽሞ እንደማይቀበሉ ያሳዩበት ድል ነዉ:: ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የራሳቸዉንና የአፍሪካንም ነጻነት ለማስከበር ያላቸዉን ቁርጠንኝነት ያመላከቱበት ድል ነዉ፡፡ ነገር ግን ለ150 ዓመታት ያህል የይህን ድል የሚመጥን ማዕከል አልነበረዉም ፡፡” ሲሉ በመደመር መንግስት መጽሃፋቸዉ አስፍረዋል፡፡

የዐድዋ ሙዝየም መፈጠር በዐድዋ መንፈስ ትዉልዱን ለመገንባት፤ የፓን አፍሪካዊነትን ስሜት ለትዉልዱ ለማስገንዝብ ይረዳል፡፡

የትዉልድ መገናኛ ማዕከል በመሆን ያገለግላል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የመላዉ ብሔር ብሔረሰቦች እና የጥቁር ህዝቦች የአይበገሬነት ታሪክ መዘከሪያ እና ማስታወሻ ማዕከል የሆነዉ የዐድዋ ሙዝየም አሁን ላይ ከመላዉ ሃገሪቱ የሚመጡ ዜጎችን ጨምሮ ከተለያዩ የአለም ክፍሎች በመጡ ታላላቅ መሪዎች፤ ተጽእኖ ፈጣሪዎች፤ አርቲስቶች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በየቀኑ ይጎበኛል፤ ይዘከራል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ሃይማኖት፤ ቋንቋ፤ ባህል፤ ታሪክ ፤ ማንነትና ባህል ቢኖራቸዉም ልዩነታቸዉ ሳያግዳቸዉ ባህር ተሻግሮ የመጣን ወራሪ ኃይል በጋራና በአንድነት እንዴት ሊመክቱ ቻሉ? ልዩነታቸዉ በአንድነታቸዉ ላይ እንዴት ተጽእኖ ሊፈጥር አልቻለም ? ልዩነታቸዉን በአንድነት ያጸኑበት ምስጢርስ ምንድነዉ? የሚሉ ጥያቄዎች አዲሱ ትዉልድ የዓድዋን ድል ሲዘክር ሊመልስና ሊማርበት የሚገባ ዋንኛዉ የአድዋ ታሪክ ነዉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review