AMN – የካቲት 16/2018 ዓ.ም
የ27ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብር ዛሬ በሚከናወን አንድ ጨዋታ ይጠናቀቃል።
በሂል ዲኪንሰን ስታዲየም ኤቨርተን ማንችስተር ዩናይትድን ምሽት 5 ሰዓት ያስተናግዳል። በቀጣይ የውድድር ዓመት በአውሮፓ መድረክ የሚያሳትፍ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ጨዋታው ለሁለቱም ክለቦች አስፈላጊ ነው።
ማይክል ካሪክን ዋና አሰልጣኝ አድርጉ ከሾመ በኋላ አስደናቂ ጉዞ ላይ የሚገኘው ዩናይትድ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ የሚያገኝበትን እድል ለማስፋት ሦስት ነጥቡ ያስፈልገዋል።
ከአራት ተከታታይ ድል በኋላ ከዌስትሃም ጋር 1ለ1 የተለያየው ዩናይትድ በዛሬ ጨዋታ ድል ከቀናው ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ይላል።
ማንችስተር ዩናይትድ በመጨረሻ ካደረጋቸው ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠመውም። 2026 ከገባ በኋላም ሽንፈት ያልገጠመው የሊጉ ብቸኛው ክለብ ነው።
በዴቪድ ሞይስ እየተመራ ከባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሻለ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ኤቨርተን የዩሮፓ ወይም ኮንፍረስ ሊግ ተሳታፊ የሚያደርገው ቦታ ይዞ ለማጠናቀቅ እየጣረ ይገኛል።
የመርሲሳይዱ ክለብ ሃሳቡን እውን ለማድረግ በሜዳው የሚያስመዘግበውን ውጤት ማሻሻል ይጠበቅበታል።
በአዲሱ ስታዲየሙ ሂል ዲክንሰን ጥሩ አጀማመር ቢያደርግም በመጨረሻ ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎቹ በአምስቱ ተሸንፏል።
ኤቨርተን ከዛሬ ተጋጣሚው ማንችስተር ዩናይትድ ጋር ጥሩ ክብረወሰን የለውም። ምንም እንኳን በዘንድሮ የውድድር ዓመት በመጀመሪያው ዙር በኦልድትራፎርድ 1ለ0 ቢያሸንፍም በአጠቃላይ ያስመዘገበው ውጤት ደካማ ነው።
ዩናይትድ በፕሪምየር ሊጉ እንደ ኤቨርተን ደጋግሞ ያሸነፈው ክለብ የለም። ቀያይ ሰይጣናቱ ኤቨርተን ላይ 42 ድል አስመዝግበዋል። ይህም በፕሪሚየር ሊጉ የትኛውም ክለብ ላይ ካስመዘገቡት ይበልጣል።
በዛሬው ጨዋታ በኤቨርተን በኩል ተከላካዩ ጃክ ኦብሪያን በቅጣት አይገባም።
በዩናይትድ በኩል ፓትሪክ ዶርጉ ፣ ማቲያስ ደሊግት እና ሜሰን ማውንት በጨዋታው የመሳተፍ እድል የላቸውም።
በሸዋንግዛው ግርማ