የብላቴ የበረሃነት ታሪክ አብቅቶ የፍራፍሬ ገነት ሆኗል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የብላቴ የበረሃነት ታሪክ አብቅቶ የፍራፍሬ ገነት ሆኗል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
  • Post category:ልማት

AMN – የካቲት 15/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሲዳማ ክልል ብላቴ አካባቢ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በጎበኙበት ወቅት፣ የአካባቢው ገጽታ ከበረሃነት ወደ ለምለም የፍራፍሬ እርሻነት መቀየሩን ገልጸዋል።

ይህ ስኬት የሰው ልጅ በርትቶ ከሰራ ተፈጥሮን መለወጥ እንደሚችል ትልቅ ማሳያ መሆኑንም አብራርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢውን ሲጎበኙ የነበረውን ምስል በማስታወስ፣ አሁን የታየውን ለውጥ አድንቀዋል፡፡

በበረሃው ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሄክታር መሬቶች በመስኖ በመታረስ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ብርቱካን፣ ሎሚ፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ሸንኮራገዳ እና አቮካዶ በስፋት እየለማ ይገኛሉ።

በክልሉ የታየው የልማት ግስጋሴ በግብርና ብቻ ሳይወሰን በሌሎችም ዘርፎች ውጤት እያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

“በሲዳማ ክልል የዶሮ ምርት ከሦስት ዓመት በፊት ከነበረበት 4 ሚሊየን አሁን ወደ 15 ሚሊየን ማደጉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያን ከድህነትና ከልመና ታሪክ ለማላቀቅ የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው በመግለጽም፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማትና በገጠር ኮሪደር የተጀመሩ ሥራዎች እርስ በርስ ሲቀናጁ የሀገርን ብልጽግና እንደሚያረጋግጡ አንስተዋል።

የአካባቢው ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክ ወደሚያስችል ደረጃ መሸጋገራቸው ትልቅ ተስፋ መሆኑንም አመላክተዋል።

እነዚህ አስተማማኝ ጅማሮዎች ተስፋፍተው ሲቀጥሉ የምናልማትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ምሶሶ ይሆናሉ በማለትም ገልጸዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review