AMN – የካቲት 18/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጀምሮ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የነበራትን ቀዳሚ ሚና በማጠናከር፣ በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል ያደረገ ስትራቴጂካዊ የዲፕሎማሲ ጉዞ እያከናወነች ትገኛለች።
በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆንዋን ተከትሎ ከዓለም ኃያላን ጋር የፈጠረችው ጥብቅ ትስስርና የዓለም መሪዎች አዲስ አበባን ተመራጭ የጉብኝት ማዕከል ማድረጋቸው፣ የአገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት አዲስ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ማሳያ ሆኗል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ናት። ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጀምሮ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችና በሌሎች መሰል የውጭ ግንኙነቶች ከፍተኛ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚና ያላት ኢትዮጵያ፣ ባለፉት መቶ ዓመታት ከተለያዩ የዓለም አገራት ጋር ጠንካራ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ገንብታለች።
በተለይ ከለውጡ ወዲህ ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሟን ማዕከል ያደረገ ከመሆኑም ባለፈ፣ ከልማት አጋርነት ወደ ስትራቴጂካዊ ትስስር መሸጋገሩን መረጃዎች ያመላክታሉ። በዚህም መሠረት ከበርካታ የአፍሪካና የዓለም አገራት ጋር የሁለትዮሽና የጋራ የልማት አጋርነት መፍጠር ተችሏል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት ካላት አህጉራዊ ሚና ባሻገር፣ የብሪክስ አባል አገራትን በመቀላቀል እንደ ሩሲያ፣ ቻይና እና ሕንድ ከመሰሉ የዓለም ኃያላን ጋር ጠንካራ ስትራቴጂካዊ ግንኙነቶችን መሥርታለች፤ ግንኙነቱንም ይበልጥ እያሳደገች ትገኛለች።

የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ፣ የቱርክዬው ፕሬዝዳንት ረጀብ ጣይፕ ኤርዶጋን፣ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ፣ የእስራኤሉ ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ለዚህ ማረጋገጫ ነው። በተጨማሪም የጎረቤት አገራት መሪዎች፣ የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ፣ የማሌዢያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቶ ሰሪ አንዋር ቢን ኢብራሂም እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ያደረጉት ጉብኝት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋነኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን የሚያጸኑ ተግባራት ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተካሄደው የቡድን 20 (G20) አባል አገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ ጥቅም የሚያጸኑ የሁለትዮሽ እና ባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን አከናውነዋል። ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም በተለያዩ የዓለም አገራት ተመሳሳይ ጉብኝትና ውይይቶችን ማድረጋቸው፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በሁሉም መስኮች ተጠናክሮ ለመቀጠሉ ትልቅ ማሳያ ነው።
እነዚህ በርካታ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ጨምሮ፣ ሌሎች ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቿን እንደሚያረጋግጡ ይጠበቃል።
በወንድማገኝ አሰፋ