የቆዳ አለርጂ መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

You are currently viewing የቆዳ አለርጂ መንስኤዎች፣ ምልክቶች እና መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች
  • Post category:ጤና

AMN- የካቲት 19/2018 ዓ.ም

የቆዳ አለርጂ ሰውነታችን የማይስማሙትን ነገሮች እንደ ባዕድ አካል በመቁጠር ለነገሩ ምላሽ ለመስጠት ሲሞክር የሚፈጠር “መቆጣት” መሆኑን በአለርት ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቆዳና አባላዘር ስፔሻሊስት ዶክተር አብዱልናስር ሀምዛ ይገልፃሉ፡፡

የቆዳ አለርጂ እንዴት እንደሚከሰት፣ እነማን ይበልጥ ተጋላጭ እንደሆኑና ስለሚደረጉ የጥንቃቄ እርምጃዎች ዶክተር አብዱልናስር ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መንስኤው

የቆዳ አለርጂ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት እንደሚችል የገለጹት ዶክተር አብዱልናስር፣ ከእነዚህም መካከል፡- የተለያዩ መድኃኒቶች፣ በቆዳ ላይ የሚቀቡ ነገሮች፣ እንደ ጆሮ ጌጥ ያሉ የብረት ውጤቶች፣ የጸጉር ቀለም እና በውስጣቸው የሚገኙ ልዩ ልዩ ንጥረ ነገሮች ይገኙበታል።

አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ለአለርጂ ቀስቃሽ ነገር ሲጋለጥ ምልክቶቹ ለመታየት ከ10 ቀናት እስከ ሁለት ሳምንት ሊፈጅ ይችላል።

ሆኖም ግን፣ ለሁለተኛ ጊዜ ሲጋለጥ ከ48 እስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ሰውነቱ ፈጣን ምላሽ ማሳየት እንደሚጀምር ዶክተሩ አስረድተዋል፡፡

ምልክቶቹ

አለርጂ በሚከሰትበት ወቅት መቅላትና ከፍተኛ የማሳከክ ስሜት፣ ሽፍታ ወይም የውሃ እብጠት፣ የተገረፈ የሚመስል ወፍራም ሽፍታ፣ አንዳንዴም መቆጣቱ በመላ ሰውነት ላይ ሊሰራጭ ይችላል።

አንዳንድ የሥራ ዘርፎች ለቆዳ አለርጂ የመጋለጥ እድልን ይጨምራሉ።

በተለይም ከውሃና ከኬሚካሎች ጋር በተደጋጋሚ የሚገናኙ ሙያዎች እንደ ጸጉር ቤት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ የሆቴልና የወጥ ቤት ሰራተኞች፣ ፈሳሽ ሳሙናዎችንና የጸጉር ቀለሞችን በተደጋጋሚ የሚጠቀሙ ሰዎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው፡፡

መፍትሄዎችና የህክምና ምክሮች

ለአለርጂ ዋነኛው መፍትሄ አለርጂውን የሚቀሰቅሰውን ነገር ለይቶ ማወቅና ከዚያ ነገር መራቅ ነው።

ባለሙያን በማማከር ከዚህ በፊት ያልተስሙንን አዳዲስ ስሜቶች/ምልክቶች ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል።

የህክምና እርዳታ፦ አለርጂው ከተከሰተ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ በህክምና ባለሙያ የሚታዘዙ የሚቀቡ ወይም የሚዋጡ መድኃኒቶችን መጠቀም ይገባል።

መከላከያ ዘዴዎች፦ ለሥራቸው ሲሉ ለኬሚካሎች ለሚጋለጡ ሰዎች እንደ ቫዝሊን፣ ፓራፊን እና ግሊሰሪን ያሉ ቅባቶችን በመጠቀም ቆዳን መከላከል ይቻላል።

መድኃኒቶችን የህክምና ባለሙያው ባዘዘው መመሪያና የጊዜ ገደብ መሰረት ብቻ መጠቀም ያስፈልጋል።

ለውጥ አግኝቻለሁ በሚል ህክምናን ማቋረጥ አለርጂው መልሶ እንዲያገረሽ ሊያደርግ ይችላል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review