• ትውልዱ ውስጣዊ አንድነትን ከሚያላላ ነገር በመቆጠብ ከዓድዋ ድል መማር እንዳለበት ተጠቁሟል
ኢትዮጵያዊነት ቅኔ ነው፤ ሰምና ወርቅ ነው። ቆላ፣ ደጋ፣ ወይናደጋ እና በረሃውን፣ ጥቁር፣ ቀይ፣ ጠይምና የቀይ ዳማውን እንደ ቡሄ ጅራፍ በወጉ ገምዶ፣ እንደ ፊደልና ቃል አዋህዶ ግሩም ትርጓሜን የያዘ ድንቅ ማንነት ነው፡፡ ለዚህ ውድ ስጦታ ኢትዮጵያውያን በየዘመናቱ በአንድነት ተምመው ዋጋ ከፍለውበታል፡፡
የዓድዋ ድል በውጫዊ የመሣሪያ፣ የፋይናንስ፣ የጦር ስትራቴጂ እና የሥልት ምክር የተደገፈ አልነበረም። ይልቅ የኢትዮጵያ ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው ችለው የመሩት፣ አንድነት እና ከምንም በላይ ሀገርን ማስቀደም ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ያረጋገጡበት ድል መሆኑን የታሪክ ባለሙያው መክብብ ንጋቱ (ዶ/ር) ይናገራሉ።
የታሪክ ባለሙያው አክለውም ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል ያደረጉበትን ምስጢርን አስመልክቶ እንደገለጹት የዓድዋ ድል ትልቁ ምስጢር ውስጣዊ አንድነት ነው፤ በዳግማዊ ምኒልክ መሪነት ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር በአንድነት፣ በሙሉ ልብና በአሸናፊነት ስሜት ወደ ጦር ሜዳው እንዲዘምቱ ተሰርቷል፡፡
ይሁን እንጂ በወቅቱ ልዩነቶች የሉም ባይባልም ኢትዮጵያውያን ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት ውስጣዊ አንድነታቸውን ከፍ አድርገው እንደ ሰርገኛ እየጨፈሩ፣ በጀግንነትም እየፎከሩ እግራቸውን ለጠጠር፣ ደረታቸውን ለጦር፣ ነፍሳቸውን ለእግዜር አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ በደም በተጻፈ ታሪካቸው ሀገር አትርፈዋል፡፡ በዓለም አደባባይም የኢትዮጵያውያንን መልክና ልክ በማይደበዝዝ ቀለም ስለዋል፡፡
በመሆኑም አዲሱ ትውልድ ከዓድዋ ብዙ የሚማራቸው ቁም ነገሮች እንዳሉ የጠቀሱት የታሪክ ባለሙያው፤ ለአብነትም ጥቃቅን ልዩነቶችን አግዝፎ ከመጣላት እና ውስጣዊ አንድነትን ከሚያላላ ነገር መቆጠብ አለበት፡፡
ሌሎች ሀገራት ዓድዋን እንደ ወርቅ በመቁጠር ተጠቅመውበታል፡፡ ነጻነታቸውንም ተጎናጽፈውበታል፡፡ እኛ ግን በልኩ ስላልተጠቀምንበት በትኩረት ልንሠራበት ይገባል፡፡ ለአብነትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለዚህ አንዱ ማሳያ እንደሆነም የታሪክ ባለሙያው መክብብ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡
ከዓድዋ ድል ማግስት አውሮፓውያኑ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ተቀብለዋል፤ ዕውቅናም ሰጥተዋል፡፡ ለአብነትም እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና መሰል ኃያላን ሀገራት በአዲስ አበባ ኤምባሲያቸውን ለመክፈት ተገድደዋል፡፡
እነዚህና መሰል ተግባራት ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብሎም በዓለም አደባባይ ገናና ስም እንዲኖራት አድርገዋል፡፡ የዓድዋ ድል ለፓን አፍሪካኒዝም መሠረት ሆኗል፤ አፍሪካ አሜሪካውያንም ነጻነታቸውን አስከብረውበታል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ይላሉ መክብብ (ዶ/ር)፤ ዘመኑን የሚመጥን ዝግጅት እና ውስጣዊ አንድነትን ማጠናከር ልክ እንደ ዓድዋ ለሁለንተናዊ ድል ያበቃል፡፡ በተለይም አርበኝነት ዘመኑ የሚፈልገውን ሆኖ መገኘት፣ ያጋጠመውን ችግር በእውቀትና ብልሃት አሸንፎም መውጣት ነውና ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ድል ይህንን ሊማሩ ይገባል ብለዋል፡፡
በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር እና ኮሙኒኬሽን መምህር ቴሶ በሪሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አንድነትና ኅብረት ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ድል ብዙ መማር አለብን። ይኸውም ለሀገር ክብርና ከፍታ ሲባል ልዩነትን በውይይትና በይቅርታ መፍታትን፣ በምትኩም አንድነትን ማጠናከር እና በጋራ በመቆም ሀገርን ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ከድሉ ብዙ ዕውቀትን መማር እንደሚቻልም ጠቅሰዋል፡፡

አክለውም ሀገር የምትገነባው የኋላውን በመያዝና ከሱም ትምህርት በመውሰድ ነው፡፡ ስለሆነም የዓድዋ ድል እንዴት እንደተገኘ? ሂደቱ ምን ይመስል እንደነበር እና የነበረው አደረጃጀትና የተከፈለው መስዋዕትነት ምን ያህል ከፍ ያለ መሆኑን በደንብ ማወቅና በዚያው ልክ ለሀገር ሁለንተናዊ ልዕልና መቆም ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ በአፍሪካውያን መዲና የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያም ትልቅ አጋዥ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ተማማ ሐጅ አደም (ዶ/ር) ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ብዙ አሰባሳቢ ትርክቶች አሏት፡፡ ለአብነትም የዓድዋ ድል አንዱ ነው፡፡ ምክንያቱም የዓድዋ ድል ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በእምነት፣ በባህል እና በቋንቋ ሳይለያዩ ከሁሉም አቅጣጫ የተሳተፉበትና ታላቅ መስዋዕትነት ከፍለው ያስገኙት ድል ነው፡፡ አክለውም ድሉ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ የተነሱበትና ነጻነታቸውን ያስከበሩበት ነው፡፡ በመሆኑም ከምንም በላይ ሀገርን ማስቀደም ከዓድዋ ድል ልንማር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዓድዋ፤ ኢትዮጵያውያን ለጋራ ዓላማ አብረው የወደቁበትና በጽናት የቆሙበት ትልቅ ተምሳሌት በመሆንም ያገለግላል። ሁሌም ኢትዮጵያውያን ለአንድነታቸው መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውንም የሚያሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የቆመችው በሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እና ሁለንተናዊ ማንነቶች ኅብረት ነው፡፡ የዓድዋ ድል ደግሞ ለዚህ ትልቅ ተምሳሌት በመሆኑ ትውልዱ ከዓድዋ በመማር ዘመኑ በሚፈልገው ልክ በተሰማራበት ሙያ ሁሉ ለሀገሩ መሥራት ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሁሉም ተጋድሎ የጸናች ሀገር መሆኗን የዓድዋ ድል ያስተምረናል። የተማረም፣ ያልተማረም፣ ገበሬውም፣ ወንዶችም፣ ሴቶችም… ሁሉም የተሳተፉበት ነው፡፡ ይህም አንዱ ያለ ሌላው መኖር እንደማይችል የሚያሳይ ነው፡፡ ደስታና ድልን፣ ሐዘንና ችግርን በጋራ ተካፍሎ መቆምን የሚያሳይ ድል በመሆኑ ዓድዋ! ለኢትዮጵያውያን ጽናትና አንድነት፤ ለሀገራዊ ዕድገትና ከፍታ ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል ተማማ ሐጅ አደም (ዶ/ር)፡፡
አክለውም ዓድዋ ያኔ! የነበረው ሕዝብ በአንድነት በመቆሙ ያስመዘገበው ድል ነው፡፡ እንዲሁም ዓድዋ ኅብረ ብሔራዊነት የተገለጠበት የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ በመሆኑም የዛሬው ትውልድ ዓድዋን የመሳሰሉና ዘመኑን የዋጁ ድሎችን በአንድነት ማስመዝገቡን ይቀጥል ዘንድ ከጥቃቅን ጉዳዮች ወጥቶ እንደ ዓድዋ ከፍ ባለ ሐሳብ ላይ አንድ መሆን እንዳለበት መክረዋል፡፡
የዓድዋ ድል ከምንም በላይ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁርጠኝነት ቆሞ የባርነት ቀንበር እንዳይጫንበት የታገለበትና ድል የነሳበት ገድል ስለመሆኑም የታሪክ ባለሙያው መክብብ (ዶ/ር) አውስተዋል፡፡
እንደ መክብብ (ዶ/ር) ገለጻ፣ አሁን ያለንበት ድህነት፣ ጉስቁልና እና አልፎ አልፎ የሚስተዋል አለመግባባት ከዚህ ቀደም በዓድዋ ላይ ከገጠመን እና ድልም ከነሳነው ችግር የሚበልጥ አይደለም፡፡ ዛሬ እያጋጠመን ላለው ችግር በመደማመጥና በመነጋገር፣ በመመካከርና በመከባበር የማይፈታ ነገር ስለማይኖር አባቶቻችን እና እናቶቻችን ያሳለፉትን ያንን ትልቅ ውጣ ውረድ መለስ ብሎ በመመልከት ትውልዱ ለሌላ ድል ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት መክረዋል፡፡ በመሆኑም ከዓድዋ ድል በጋራ መቆምን፣ በጋራ ማቀድን፣ በጋራ መተግበርን መማር አለብን፡፡

ስለ ዓድዋ ከተጻፉ መጻሕፍት መካከል የዓድዋ ጦርነት (THE BATTLE OF ADWA) የተሰኘው መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ ይህንን ድንቅ መጽሐፍ ለሕትመት ያበቁት የታሪክ ተመራማሪዎቹ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ዘውዴ ገብረ ሥላሴ፣ ንጉሤ አየለ፣ ሃሮልድ ማርከስን የመሳሰሉ ጉምቱ የታሪክ ምሁራን ናቸው፡፡
በመጽሐፉ የዓድዋ ድል በጣፋጭ ቃላት ተውቦ ይታያል፡፡ ዓድዋ የድፍረት፣ የድል እና የኩራት ተምሳሌት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም ላይ የተቀዳጀችው የዓድዋ ድል የሰው ልጆች ሁሉ እኩል መሆናቸውን በሚገባ ያረጋገጠ ዝንፍ የማይል መለኪያ ነው፡፡ ዓለማችን ግሩም የታሪክ እጥፋት ያስመዘገበችበት ወሳኝ የታሪክ ክስተትም ነው ዓድዋ!
ዓድዋ የዓለማችን ድንቅ የታሪክ ዘለላ ሲሆን፣ በተለይም የመላው አፍሪካውያን የጋራ ትውስታቸው ስለመሆኑም በመጽሐፉ የተለያዩ ገጾች በወጉና በልኩ ተመላክቷል፡፡ ይህም በመሆኑ ዓድዋ በዘመን ጅረት ሳያረጅ ሰርክ አዲስ እንደሆነ እና ሁሌም እንደተከበረ በአፍሪካውያን ሰማይ ሥር እንደ ፀሐይ ፈክቶ ዓለምን በእኩልነት ፀዳል እያጥለቀለቀ በከፍታ የሚኖር ታላቅ ድል ስለመሆኑም ተጽፏል፡፡
በመጽሐፉ በግልጽ እንደተመላከተው ዓድዋ ከትውስታ በላይ ነው፡፡ ድል የተፈጸመበትን ዘመን ብቻ የሚናገር፣ ተደምጦም የሚቀር አይደለም፡፡ ይልቅ ዓድዋ ሁሌም እንደ ንጋት ኮከብ እያበራ እና በዓለም የታሪክ ምዕራፍ ላይ ሰርክ አዲስ እንደሆነ ይቀጥላል እንጂ፡፡ አዎ! ዓድዋ ጊዜውን የሚያንጸባርቅ ድል ብቻ ሳይሆን “የሰው ልጆች ሁሉ እኩል ናቸው!” እያለ በእውነት አደባባይ ከአድማስ አድማስ፣ ከዘመን ዘመን የሚመሰክር ድል ነው፤ ዓድዋ!
በእርግጥም በዓድዋ በተካሄደው ጦርነት ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያደረጉት ተጋድሎና ያስመዘገቡት ድል የኢትዮጵያ ነጻነትና ሉዓላዊነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ከማስቻሉም ባለፈ በወቅቱ በቅኝ ገዢዎች ተይዘው በባርነት ቀንበር ሲማቅቁ የነበሩ አፍሪካውያን ለሚያደርጉት የነጻነት ትግል ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ ነው፡፡ በርካታ አፍሪካውያንና የታሪክ ጸሐፍትም የዓድዋ ድልን “የአፍሪካ ድል”፣ “የእኩልነትም ቀንዲል!” እያሉ ይጠሩታል፡፡
ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ እስከ ካራማራ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሀገራቸውን በአጥንታቸው አጥረው አስከብረዋል፡፡ ሉዓላዊነትን እና ነጻነታቸውን ለማስጠበቅ ከተከፈለው ዋጋ ባልተናነሰ መልኩ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በመሳሰሉ ከፍ ከፍ ባሉ ልማቶች ያለምንም ልዩነት ተሳትፈው የአብሮነት ክንዳቸው ምን ያህል ብርቱ እንደሆነም አሳይተዋል፡፡
የታሪክ ባለሙያው መክብብ ንጋቱ (ዶ/ር) አክለውም ዛሬም ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ድል ትምህርት በመውሰድ የሀገርን ሁለንተናዊ ልማትና ከፍታ በሚያረጋግጡ ልማቶችና ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ በአንድነት በመቆም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ከፍታ ማስቀጠል ይጠበቅብናልም ብለዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ