AMN- የካቲት 22/2018 ዓ.ም
ታላቁ የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል እና የኢትዮጵያዊነት ጥንካሬ ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገራችንን ወደ ዘመናዊነት ያሸጋገረ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
ዛሬም ይህ ድል በልማት እና በኢኮኖሚ ነጻነት ሊደገም እንደሚገባው ምሁራን ያሳስባሉ።
የነጮች የበላይነት በነገሰበት እና ጥቁሮች በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት ለባርነት በሚታጩበት በዚያ የቅኝ ግዛት ዘመን፣ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ደረታቸውን ለጥይት የሰጡበት የጽናት እና የአንድነት ውጤት የሆነው ታላቅ ድል በአድዋ ተራሮች ላይ እንዲጻፍ አደረገ።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ማናዬ ዘገየ እንደሚሉት፣ አድዋ ለኢትዮጵያ የዘመናዊነት ምዕራፍ መጀመሪያ ነው።
አባቶቻችን እንዲህ አይነት ዋጋ ባይከፍሉ ኖሮ እንደ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች በባዕድ ቋንቋ እና በባህል ተጽእኖ ስር እንወድቅ ነበር ሲሉ የድሉን ፋይዳ ያስረዳሉ።
ዶክተር ማናዬ አክለውም፣ የአድዋ ጀግኖች የነበራቸውን ሃይማኖታዊ፣ ብሔራዊ እና ባህላዊ ልዩነት በአንድነት በማስተሳሰር ለጠላት የማይመች ግንብ መገንባታቸውን ገልጸዋል።
ይህ አንድነት ነው ዛሬም ለሀገራችን ህልውና መሰረት የሆነው ብለዋል።
አንድ መቶ ሰላሳ ዓመታትን ያስቆጠረው የአድዋ ድል በታሪክ መዝገብ ብቻ ተወስኖ መቅረት የለበትም የሚሉት ዶክተር ማናዬ፣ የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ጀግንነት በኢኮኖሚ ማንሰራራት በማስቀጠል ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ መልክዓ ምድር፣ አየር ንብረት እና አምራች ኃይል በመጠቀም ድህነትን መርታት እንደሚገባው ያነሳሉ።
ከውጭ የምናስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ በመተካት እና በፖሊሲ የታገዘ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መገንባትም እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ።
ዛሬ ጦርነታችን ከድህነት ጋር ነው የሚሉት ዶክተር ማናዬ፣ ዘረኝነት እና አካባቢያዊነትን በማስወገድ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነትን መገንባት የአድዋ አደራ ተቀባይ መሆን እንደሆነም ገልጸዋል።
ልማት፣ ብልጽግና እና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የዚህ ታላቅ ታሪክ ቀጣይ ምዕራፎች እንደሆኑም ተናግረዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ