ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ጋር ተወያዩ

You are currently viewing ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ጋር ተወያዩ

AMN ግንቦት 7/2018

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ከቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ከውይይቱ በኋላ የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቢግ ዊን ፊላንትሮፒ በአፍሪካ የሕፃናትና ወጣቶችን ሕይወት ለማሻሻልና የወደፊት አቅማቸውን ለመገንባት በቁርጠኝነት የሚሠራ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።

ከፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ጋር ባደረጉት ውይይት ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ባለው ጠንካራ አጋርነት እና በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ በሚደግፏቸው ፕሮጀክቶች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አዲስ አበባ በቀዳማይ ልጅነት (Early Childhood) ልማት ዙሪያ ለአፍሪካ አህጉር ትልቅ ምሳሌ መሆን መቻሏን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ከአሥራ ዘጠኝ ሀገራት የተውጣጡ አካላት መጥተው የአዲስ አበባን ተሞክሮ መውሰዳቸውን ለፕሬዝዳንቱ ማብራራታቸውን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ስኬታማ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ መካሄዱን ተናግረዋል።

ቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበትና በትብብር እንደሚሠራ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በጋራ የተያዙ ሀገራዊ ግቦች በውጤታማነት እንዲከናወኑ ድርጅታቸው የበኩሉን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

ፋውንዴሽኑ በአሁኑ ወቅት በቀዳማይ ልጅነት ዕድገትና እንክብካቤ ዙሪያ፣ በሕፃናትና ወጣቶች ሥነ-ምግብ ማሻሻል ላይ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን በማገዝ እንዲሁም የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን በማሻሻል ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ከተሞችን ፈጣን ዕድገት ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማረጋገጥ እንዲቻል፤ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ እና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ድርጅታቸው ጠንካራ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review