የካቲት 22/2018 ዓ.ም
የዓድዋ ጀግኖች ከ130 ዓመታት በፊት የሐገራቸውን ሉዓላዊነት እና ነጻነታቸውን ለማስከበር በከፈሉት መስዋዕት የተመዘገበው አኩሪ ድል ከኢትዮጵያ እና አፍሪካ አልፎ የዓለም መነጋሪያ ሆኖ ነበር፡፡
በርካታ የአፍሪካ እና የዓለም ሐገራት መሪዎች፤ ፖለቲከኞች፤ ምሁራን፤ የኪነ ጥበብ እና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ስለሆነው የዓድዋ ድል ብዙ ተናግረዋል፤ ጽፈዋል፤ አዚመዋል፤ ስለዋል በተለያዩ መንገዶች አድናቆታቸውንም ገልጸዋል፡፡
የዓድዋ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ያለምንም የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ ፣ የጾታ እና ማንነት ልዩነት በጋራ ከቆሙ ያቀዱትን መፈጸም እንደሚችሉ፣ ጠንካራ የጽናት ፣ የአሸናፊነት እና የአይበገሬነት መንፈስ ለቀጣዩ ትውልድ አውርሰው አልፈዋል፡፡

የዓድዋ ጀግኖች አኩሪ ድል በመላው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ በሐገር ውስጥ እና በውጭ ሐገራት ጭምር በየዓመቱ ይዘከራል፡፡ 130ኛው የዓድዋ ድልም በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየታሰበ ይገኛል፡፡
በዓሉ በተለይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በአዲስ አበባ መሃል ፒያሳ ላይ ከተገነባ ወዲህ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ይገኛል፡፡ አዲሱ ትዉልዱም የአባትና እናት አርበኞቹን ተጋድሎ በአግባቡ እንዲረዳ ትልቅ እድል ፈጥሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመደመር መንግሥት መጽሃፋቸዉ እንዳሰፈሩት”ዐድዋ አፍሪካዊያን ቅኝ ግዛትን ፈጽሞ እንደማይቀበሉ ያሳዩበት፤ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የራሳቸውን እና የአፍሪካንም ነፃነት ለማስከበር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያመላከቱበት ድል ነዉ፤ ነገር ግን ለ150 ዓመታት ያህል ይህን ድል የሚመጥን ማዕከል አልነበረዉም “ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የዓድዋ ሙዝየም ግንባታ ከአካባቢው ጋር በመሠናኘቱ ዓድዋ ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርጓል፡፡ የዓድዋ ሙዝየም መፈጠር በዓድዋ መንፈስ ትውልዱን ለመገንባት፤ የፖን-አፍሪካዊነትን ስሜት ለትውልዱ ለማስገንዘብ አግዟል፡፡ የትዉልድ መገናኛ ማዕከል በመሆንም እያገለገለ ይገኛል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያ አሁን ላይ ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ውበት ከማላበሱም በላይ በርካታ የሐገር ውስጥ እና የውጭ ሃገር ጉብኝዎች በየቀኑ የሚጎበኙትና ሊጎበኙት የሚመርጡት ትክክለኛ የዓድዋ ጀግኖች መዘከሪያ ማዕከል ሆኗል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ