ዓለም ስለ አድዋ ምን አለ? ከለንደኑ ዘ ታይምስ እስከ ኔልሰን ማንዴላ የተሰጡ ምስክርነቶች

You are currently viewing ዓለም ስለ አድዋ ምን አለ? ከለንደኑ ዘ ታይምስ እስከ ኔልሰን ማንዴላ የተሰጡ ምስክርነቶች
  • Post category:ታሪክ

AMN- የካቲት 24/2018 ዓ.ም

መላው ኢትዮጵያውያን በ1888 ዓ.ም ሀገር ሊወር የመጣውን ፋሺስት በአድዋ ተራራዎች ላይ ድል ነስተዋል።

ይህ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል መነሻ ሆኗል።

የደቡብ አፍሪካው የነፃነት አባት እና ከአፓርታይድ አገዛዝ በኋላ የሀገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ “ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ፋና ወጊ ናት፤ የአድዋ ድል ደግሞ አፍሪካውያን በራሳቸው መተማመንን እንዲያገኙ ያደረገ ታላቅ ታሪካዊ ክስተት ነው” ብለዋል።

የኬንያ የነፃነት ታጋይ እና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ በበኩላቸው፤ “ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ መቆየቷ ለእኛ ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ ኩራት እና የትግል አርአያ ሆኖናል” በማለት የአድዋን ድል ታላቅነት ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የጋናው የነፃነት አባት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መስራች ክዋሜ ኒክሩማ ፦ “ኢትዮጵያ ያልተንበረከከች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር መሆኗ ለእኛ ለሌሎች አፍሪካውያን የነፃነት ተስፋችንን እንድናለመልም አድርጎናል” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የጥቁር ህዝቦች መብት ተሟጋች እና የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ ጃማይካዊው ማርከስ ጋርቬይም ኢትዮጵያን የነፃነት ምድር አድርጎ ይቆጥራታል።

የአድዋን ድል ሲገልጽም፦ ”ጥቁር ህዝቦች ሆይ ወደኋላ ተመልከቱ! ኢትዮጵያ በአድዋ ያሳየችው ጀግንነት የእናንተም ጀግንነት ነው“ ብሏል።

ስለ ጥቁር ህዝቦች ታሪክ እና የነፃነት ትግል በርካታ መጽሐፍትን የደረሱት አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ሞሌፊ ኬቴ አሳንቴ በአድዋ ላይ ባላቸው እይታ፦ አድዋ ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ማረጋገጫ ነው።

አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ሲነሱ አድዋ ‘አትችሉም’ የሚል ትልቅ ግድግዳ ሆነባቸው” ብለዋል።

ሌላኛው ጥቁር አሜሪካዊ ምሁር ዶክተር ደብሊው ኢ ቢ ዱቦይስ በበኩላቸው፦ አድዋ የአውሮፓን የበላይነት ትረካ የሰበረ ታላቅ ክስተት ነው።

ይህ ድል ለአለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ተስፋን የሰጠ እንጂ የኢትዮጵያ ብቻ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ሲሉ አክለዋል።

በወቅቱ የነበሩ የምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙሃንም ለአድዋ ድል ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ዘግበዉ ነበር።

በፍሬሕወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review