የስፖርቱ አዲስ ምዕራፍ

You are currently viewing የስፖርቱ አዲስ ምዕራፍ

ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ዓለም ስሟ በወርቅ ቀለም ቢጻፍም፣ የዓለም የአትሌቲክሱ ኮዋክብት የኢትዮጵያን ምድር ሲረግጡና ከጀግኖች አትሌቶች ጋር ሲወዳደሩ ማየት ለብዙ ዘመናት የተናፈቀ ህልም ነበር። አሁን ግን ያ ህልም እውን ሊሆን አዲስ አበባ የዓለም አትሌቲክስ መዲና ልትሆን ለሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ተቆርጦለታል። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም አቀፍ የአንድ ቀን ውድድር (One Day Meeting) አዘጋጅ ለመሆን በዓለም አትሌቲክስ ካላንደር ውስጥ በይፋ ተካትታለች።

የኢትዮጵያ የአዘጋጅነት ጉዞ ስኬታማ ሊሆን የቻለው በዘፈቀደ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች በተረጋገጠ ተግባራዊ ዝግጁነት ነው። የዓለም አትሌቲክስ የውድድሮች ዳይሬክተር ፒርስ ኦካላጋን በአዲስ አበባ ባደረጉት የዳሰሳ ጥናት፣ ሀገሪቱ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን የማሟላትና ታላላቅ ውድድሮችን በብቃት የማዘጋጀት አቅም እንዳላት መስክረዋል።

ውድድሩን ፍጹም ስኬታማ ለማድረግም ከዓለም አቀፍ የቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር በቅርበት እየተሰራ ይገኛል። የዓለም አትሌቲክስ በጉዳዩ ላይ በሰጠው አስተያየት፣ ኢትዮጵያ ለዓለም አትሌቲክስ እድገት ያበረከተችው አስተዋጽኦ ወደር የለውም። አዲስ አበባን በዓለም አቀፍ የውድድር ካላንደር ውስጥ መካተቷም፣ ስፖርቱን በዓለም ዙሪያ ተደራሽ ለማድረግ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ስኬት ነው ብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ዕድል በማግኘቷ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት “የዓለም አቀፍ ግንኙነትና የስፖርት ዲፕሎማሲ እና የስፖርት መሰረተ ልማት መስፋፋት ስራችን ፍሬ እያፈራ ይገኛልም” ሲሉ አስፍረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ ፌዴሬሽኑ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር የጀመረውን የስፖርት ዲፕሎማሲ ወደ ከፍታ በማድረስ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ውድድር ለማዘጋጀት በማስቻል አዲስ ምዕራፍ አስመዝግቧል ብሏል። የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዋና ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የሁለት ቀን የስራ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት በቂ አቅም እንዳላትና የተለያዩ ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ እናስመጣለን ማለታቸው የሚታወስ ነው። ውድድሩን የዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚመሩት በመሆኑ የአትሌቲክስ ሙያተኞች ልምድ ለማግኘት የሚያስችልና ከተለያዩ ሀገሮች የተወጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉበት ከመሆኑ ባሻገር በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት የሚያገኙበት ይሆናል።

የዓለም አትሌቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው ውድድሩ እንደ ዓለም ሻምፒዮና ወይም ኦሎምፒክ በአንድ ወቅት ተከብሮ የሚያልቅ ሳይሆን፣ በየዓመቱ በተለያዩ ከተሞች የሚዘዋወር የሊግ ውድድር አካል ነው። በውድድሩ ላይ በዓለም ደረጃ ታዋቂ የሆኑ አትሌቶች የሚሳተፉበትና በሰዓትና በነጥብ የሚፎካከሩበት መድረክ ነው። ውድድሩ በዓለም አቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ የሚተላለፍ በመሆኑ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ዘንድ ይደርሳል።

ይህ ታሪካዊ አጋጣሚ ከስፖርታዊ ትንቅንቅ ባለፈ፣ ለሀገሪቱ የገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ መነቃቃት የያዘው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው። ታዋቂው ኬንያዊ የስፖርት ጋዜጠኛ እና በዓለም አትሌቲክስ ዘንድ ከፍተኛ እውቅና ያለው ኢልያስ ማካሪ፣ አዲስ አበባ ለዚህ ውድድር መመረጧን ሲገልጽ፣ “አዲስ አበባ ይህን ዕድል ማግኘቷ አትሌቲክሱን ወደ ቤቱ የመመለስ ያህል ነው” በማለት ገልጿል።

በአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት ግዙፍ የሜጋ ፕሮጀክቶችና የስፖርት መሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ኢትዮጵያ ይህን ታሪካዊ ዕድል እንድታገኝ የነበረው አስተዋጽኦ የጎላ ነው። የዓለም አትሌቲክስ (World Athletics) አንድን ከተማ ለአዘጋጅነት ከመምረጡ በፊት የሚመለከተው፣ “ስታዲየሙ የት ነው?” የሚለውን ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የከተማዋን ዝግጁነት ጭምር ነው። እንደዚሁም ከዋናው ስታዲየም ጎን ለጎን የተገነቡት የመለማመጃ ሜዳዎች አትሌቶች ያለምንም እንግልት ለውድድር እንዲዘጋጁ ስለሚረዱ ለምርጫው ትልቅ ክብደት ሰጥተውታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የሰራቸው በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት ተደርገዋል፡፡ መሰረተ ልማቶቹም እግር ኳስ ሜዳ፣ መሮጫ ትራክ፣ 3 በ 1 ሜዳ፣ 2 በ 1 ሜዳ እና ስኬት ቦርድን ያካትታሉ፡፡

በካዛንቺስ መልሶ ማልማት እየተገነባ ያለውና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘነው በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የተለያዩ ዘመናዊና ባህላዊ ስፖርትን የያዘ ስፖርት ፓርክም አዲስ አበባ ከከተማ አልፎ ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም የምታበረክተው ዋንኛው የስፖርት መሰረተ ልማት ነው፡፡ በዚህም አዲስ አበባ በንግድ እንቅስቃሴዋ ብቻ ሳይሆን በስፖቱም ዘርፍ ክረምት ከበጋ በቀንና በምሽት የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚከወኑባት ዘመናዊ መዲና ሆናለች፡፡

በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለስፖርት ዲፕሎማሲው ትልቅ አቅም የፈጠረ ሲሆን፣ ስታዲየሞችን ከኤርፖርትና ከትላልቅ ሆቴሎች ጋር የሚያገናኙ ሰፋፊ መንገዶች መገንባታቸው፣ ለልዑካን ቡድኖችና ለጋዜጠኞች የተቀላጠፈ እንቅስቃሴን ያረጋግጣል።

አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ሆቴሎች መናኸሪያ መሆኗ፣ የአትሌቶችን አመጋገብ፣ እረፍትና ደህንነት ለመጠበቅ አስተማማኝ ዋስትና ሆኖ ቀርቧል። “ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዛሬ ላይ ከሜዳው ብቃት ባለፈ የመሠረተ ልማት ዝግጁነትን በእጅጉ ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከተማ ውበትና በስታዲየም ግንባታ ላይ ያሳየችው ግስጋሴ፣ የዓለም አትሌቲክስ ኃላፊዎች አዲስ አበባ አሁን ዝግጁ ናት” የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ እንዳደረጋቸውም ተገልጿል።

በውድድሩ ላይ ሊሳተፉ የሚችሉ ኮከቦችን መገመት ከወዲሁ አጓጊ ሲሆን አዲስ አበባ በከፍታ ቦታ ላይ የምትገኝ በመሆኑ፣ ውድድሩ በተለይ በረጅም እና በመካከለኛ ርቀት ሯጮች መካከል ከፍተኛ ትንቅንቅ እንደሚታይበት ይጠበቃል። ይህ ውድድር የዓለም አትሌቲክስ ካላንደር አካል በመሆኑ፣ ታዋቂ የውጭ ሀገር አትሌቶች ነጥብ ለማግኘትና ታሪክ ለመስራት ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸው አይቀርም።

ኢትዮጵያ የአትሌቲክስ መገኛ ከመሆኗም በተጨማሪ አዳዲስና ዘመናዊ የስፖርት መሠረተ ልማቶች መስፋፋት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል የሚለው ደግሞ የስፖርት ባለሙያው ይድነቃቸው ግርማ ነው፡፡ በመዲናዋ የአትሌቲክስ ስፖርት አሰልጣኝ የሆነው ይድነቃቸው እንደሚለው ይህ ውድድር ኢትዮጵያ ከአትሌት አምራችነት ባለፈ፣ ዓለም አቀፍ ክስተቶችን በብቃት መምራት የምትችል ተደማጭ ስፖርታዊ ኃይል መሆኗን የምታስመሰክርበት ወርቃማ አጋጣሚ ነው። በስፖርት ዲፕሎማሲ ስሌት፣ አንድ ስኬታማ ውድድር በመቶዎች የሚቆጠሩ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ያጠነክራል፤ ሀገሪቱ ለዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ያላትን ተመራጭነትም በተግባር ያረጋግጣል ይላል አሰልጣኝ ይድነቃቸው፡፡

ይህ ውድድር ከስፖርት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ያሉት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ‘የአትሌቶች ምድር’ ብትባልም፣ ዓለም አቀፍ አድናቂዎች አትሌቶቻችንን በሀገራቸው መሬት ላይ ሲሮጡ የማየት ዕድል አልነበራቸውም። ውድድሩ አዲስ አበባን በስፖርት ቱሪዝም ካርታ ላይ ከማውጣቱም ባሻገር በመቶዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች፣ አሰልጣኞች፣ ጋዜጠኞችና ቱሪስቶች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ሆቴሎች፣ ትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች ገቢ ያገኛሉ።

ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚቀጠሩ ባለሙያዎችና ለዝግጅቱ የሚውሉ ግብዓቶች ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ውድድሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማካሄድ ስታዲየሞች፣ የመለማመጃ ሜዳዎችና የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን ስላለባቸው፣ ሀገሪቱ ዘመናዊ የስፖርት ቁሳቁስ ባለቤት እንድትሆን ዕድል ይፈጥራል የሚለውም የባለሙያው አስተያየት ነው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review