AMN – የካቲት 28/2018 ዓ.ም.
ለ7ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዘገባ ዛሬ የካቲት 28 ይጀመራል፡፡ ማንኛውም ሰው የሚፈልገውን ፓርቲ ወይም ዕጩ ተወዳዳሪ ለመምረጥ የሚችለው በቅድሚያ በመራጭነት ሲመዘገብ ብቻ ነው፡፡ በመራጭነት ሳይመዘገብ ቀርቶ በምርጫው ዕለት መራጭ ሆኖ መቅረብ አይችልም፡፡ ድምጽዎ ዋጋ አለውና ተመዝግበው የመራጭነት ካርድዎን ይያዙ፡፡
በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያበቁ መመዘኛዎች ምንድን ናቸው?
በአዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት በማንኛውም ምርጫ የሚሳተፈው ሰው የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርበታል፦
ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው
በምዝገባው ዕለት ዕድሜው/ዋ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነ/ች
ለምዝገባ በቀረበበት የምርጫ ክልል ቢያንስ ለ6 ወራት የኖረ ሰው መሆን፡፡

መመዝገብ የማይችሉት እነማን ይሆኑ?
በአዕምሮ ሕመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ የሚታወቅ ሰው
በፍርድ የተወሰነበትን የእስራት ቅጣት በመፈጸም ላይ ያለ ሰው
የመምረጥ መብቱ በሕግ የተገደበበት ሰው በመራጭነት ለመመዝገብ እንደማይችል በሕጉ ተደንግጓል፡፡
ለምዝገባ ወደ ምርጫ ጣቢያ ሲኬድ መያዝ የሚያስፈልጉ ሰነዶች ምንድን ናቸው?
በምርጫ ጣቢያው ክልል ውስጥ ነዋሪ መሆኑን የሚገልጽ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት፤
ከነዚህ አንዱም ከሌለ ሌሎች የማንነት መግለጫ ሰነዶችን (መንጃ ፈቃድ፣ የመኖሪያ የምስክር ወረቀት፣ በተባበሩት መንግስታት የተሰጠ የስደተኛ ካርድና የመሳሰሉት) መያዝ
የቀበሌ መታወቂያ ካርዱ ወይም ፓስፖርቱ ያልታደሰ ቢሆንም እንኳን ለምዝገባ ሊያገለግል ይችላል
የተጠቀሱት ሰነዶች ባይኖሩም ለመመዝገብ የቀረበውን ሰው መዝጋቢዎቹ በአካባቢው ነዋሪ መሆኑን ለይተው የሚያውቁት ከሆነ ወይም በምርጫ ጣቢያው በሕዝብ የተመረጡ የሕዝብ ታዛቢዎች የሚያወቁት ከሆነ በቃለ-ጉባዔ ተይዞ መመዘገብ ይችላል፡፡

በዲጂታል አማራጭ ለመመዝገብስ መን ያስፈልጋል?
“ምርጫዬ” የተሰኘውን የመራጮች መመዝገቢያ መተግበሪያ ከPlay Store / APP Store ማውረድ
የፋይዳ መታወቂያዎት 16 አኅዝ ቁጥር (FAN) በማስገባት መመዝገብ
ከመተግበሪያው የሚኣገኚትን ቋሚ የመራጭነት መለያ ቁጥር መመዝገብ ያስፈልጋል
“ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይመዝገቡ” የሚለውን በመጫን ምዝገባዎትን ማጠናቀቅ
በዝርዝሩ ውስጥ ከሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የሚቀርብዎትን የምርጫ ጣቢያ በመምረጥ “ይመዝገቡ” የሚለውን በመጫን በምርጫ ክልሉ በነዋሪነት የቆዩበትን ጊዜ ማስገባት
የመረጡትን መታወቂያ ፊት እና ጀርባ ፎቶ ማንሣት እና ማያያዝ
በምርጫ ቀን ይዘው የሚመጡት ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል የምርጫ ካርድ ከ48 ሰዓት በኋላ ከመተግበሪያው ያገኛሉ
ዋናው ገጽ ላይ በመመለስ የምርጫ ካርድዎትን “ያትሙ” የሚለውን አማራጭ በመጫን መያዝ ይኖርብዎታል።
በመራጭነት የተመዘገበ ሰው ሊሰረዝ ይችላል?
በመራጭነት የተመዘገበ ሰው በአዕምሮ ሕመም ምክንያት ለመወሰን ብቃት የሌለው ሆኖ የተገኘ ወይም በማጭበርበር የተመዘገበ ወይም የሞተ ወይም የተፈረደበት ካልሆነ በስተቀር በማናቸውም ሌላ ምክንያት ከመራጭነት መዝገብ አይሰረዝም፡፡