ከዓሣ አጥማጆች መንደር እስከ “የዓለም የሳይክል መዲና”

You are currently viewing ከዓሣ አጥማጆች መንደር እስከ “የዓለም የሳይክል መዲና”
  • Post category:ታሪክ

AMN- የካቲት 30/2018 ዓ.ም

“ከተማ የሕንፃ ብዛት ብቻ የሚታይበት ሳይሆን ፣ የሰው ልጅ ተስፋና ትጋት የሚተነፍስባት ታላቅ መድረክ ነው ።

በከተሞች ጎዳና የሺዎች ህልም ይሸመናል፤ በህንፃዎቻቸው ጥላ ስርም የታሪክና የሥልጣኔ አሻራዎች ይኖራሉ። እያንዳንዱ ከተማ የራሱ የሆነ የልብ ትርታ ያለው ሲሆን፣ ነዋሪዎቿ ደግሞ ያንን ትርታ ሕያው የሚያደርጉ የከተማዋ ነፍሶች ናቸው።

ከተሞችን የሚገነቡት የሰው ልጆች ቢሆኑም፣ ከተሞችም መልሰው የሰው ልጆችን ማንነትና የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀረፅባቸው የጥበብ ማዕከላትና መዳረሻ ናቸው ።”

ታዲያ በዛሬ የከተሞች ተሞክሮ ፅሁፋችን ከአውሮፓ ከተሞች መካከል በተፈጥሮ ውበት፣ በሳይክል እና በእግረኛ መንገድ ምቾት፣ እንዲሁም በቱሪዝም ቀዳሚ የምትባለውን የዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገንን (Copenhagen) መርጠን መረጃዋን ልናጋራችሁ ወደናል ።

ከተሞች የራሳቸው የሆነ ልዩ መገለጫ አላቸው ታዲያ ያንዳንዶቹ ደግሞ ከመገለጫነት አልፎ ለሌሎች በአብነት በሚጠቀስ ስራዎቻቸው እንዲታወሱ ያደርጋቸዋል ።

ኮፐንሃገን፡ ከዓሣ አጥማጆች መንደር እስከ “የዓለም የሳይክል መዲና” የኮፐንሃገን ምስረታ በ12ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በኤጲስ ቆጶስ አብሳሎን አማካኝነት እንደ አንድ ምሽግ መመስረቷን ታሪክ ያስረዳል። ይህች ከተማ የወቅቱ ስሟ “ኮፕማንሃቭን” (Køpmannæhafn) ሲሆን ትርጓሜውም “የነጋዴዎች ወደብ” ማለት ነው ሲሆን በባህር ዳርቻ ላይ በመገኘቷ ለዓሣ ማጥማድና ለንግድ ምቹ እንደነበረች ታሪክ ያወሳል ።

በዚህ መልክ የተመሰረተችው ከተማ በ17ኛው ክፈለ ዘመን በንጉስ ክርስቲያን 4ኛ ዘመን (የከተማዋ ዋና መሃንዲስ ተብለው በሚጠሩት)፣ ኮፐንሃገን ዘመናዊ መልክ መያዝ የጀመረች ሲሆን አሁን ላይ በከተማዋ የቱሪስቶች መዳረሻ የሆኑትን እንደ ኒሃቭን (Nyhavn) ያሉ ውብ የውሃ ዳርቻ ቦዮች እና ታሪካዊ ህንፃዎች ተጠቃሽ ናቸው ።

ታዲያ ጥንታዊ የሰልጣኔ መሰረት ያላት ከተማ በትላንት ታሪኳና ቅርሶቿ ታጥራ አልተቀመጠችም የከተማን ትክክለኛ ትርጉም የክት አድርጋ ከዘመኑ ጋር አብራ እየዘመነች ያለች ከተማ ሆናለች ።

የኮፐንሃገን ታላቁ የለውጥ ምዕራፍ እና ለሰው ልጅ ምቹ መሆን ከ1960ዎቹ እስከ ዛሬ

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ሁኔታ የተነቃቃበት ጊዜ ነው ብዙ ከተሞችም ለመኪናዎች ቅድሚያ የሰጡበት ጊዜ ነው ፣ ነገር ግን ኮፐንሃገን የሌሎቹን ከተሞች ፈለግ አልተገበረችም ይልቁንም የተለየ መንገድ መረጠች።

በ1962 ዓ.ም “ስትሮጌት” (Strøget) የተባለው የከተማዋ ረጅም መንገድ ለመኪና ዝግ ሆኖ ለእግረኞች ብቻ ተከፈተ በዚህም ሃገሪቱ የእግረኛ መንገድ አብዮት አስጀመረች ። ይህ ትግበራ በወቅቱ ትልቅ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ ዛሬ ግን የከተማዋ የንግድ እና የቱሪዝም የልብ ትርታ እና ለተቀረው ዓለም ምሳሌ ሆኗል።

በኮፐንሃገን ጎዳናዎች ዜጎች በሳይክል መንቀሳቀስ እንደኛ ሀገር ገበታን ያለእንጀራ እነደለማሰብ ባህል ሆኗል። ከተማዋ በልዩ ሁኔታ ለሳይክል ተጓዦች ተለይተው የተገነቡ ሰፊ የመንገድ መሰረተ ልማት አሏት። አሁን ላይ ከ60% በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ለስራና ለትምህርት የሚንቀሳቀሱት በሳይክል ነው።

ሌላኛው የከተማዋ መገለጫ ተፈጥሮ እና ዘመናዊ መዝናኛ ነው።
ኮፐንሃገን “አረንጓዴ ከተማ” ለመሆን ድንቅ ስራዎች አከናውናለች በዚህም እንደ “ቲቮሊ ጋርደን” (Tivoli Gardens) ያሉ ጥንታዊና ዘመናዊ መዝናኛዎችን የያዙ የከተማ መናፈሻዎች ፓርኮች በከተማዋ መሃል ይገኛሉ።

እንዲሁም የከተማዋ የባህር ዳርቻ ውሃ በጣም ንጹህ በመሆኑ የነዋሪዎችና የቱሪስቶች ቀልብ ከመሳቡ በላይ በከተማው መሃል በዋና የሚዝናኑባት ከተማ ለመሆን አስችሏታል።

ታዲያ ከተሞችን ስናስብ ወደ አዕምሯችን የሚመጣውን ሰማይ ጠቀስ ህንፃና የትልልቅ ኢንዲስትሪዎች ማዕከል መሆን ብቻ ሳይሆን ለነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የተመቸ አኗኗር ምክኒያት እንዲሆኑ የሚያስችል ተግባራት በመከወን የኮፐንሃገን ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው ።

ታዲያ ከተመሰረተች ከ130 ዓመታት በላይ ያስቆጠረችው መዲናችን አዲስ አበባ የዓመታት የቤት ስራዋን አሁን ላይ እየመለሰች ትገኛለች ወንዞቿ ይቀር አንደ ኮፐንሃገን ይቅር ቱሪስቶች ሊዋኙባቸው ነዋሪዎች በእነሱ አካበቢ ለማለፍ የሚሳቀቁባቸው እንዲሁም ጎዳናዎቿ መኪናና እግረኛ እየታከኩ የሚጓዙባቸው ጠባብ ጎዳና መገለጫዎቿ አሁን ላይ ዘምነውና አምረው ተሰርተዋል ።

አሁን ላይ አዲስ አበባ ዓለም ዓቀፍ ከተማነቷን የሚመጥን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች-በኮሪደር ልማት የለሙ ሰፋፊ እና ዘመናዊ የመኪና መንገድ እና የሳይክል መሰረተልማቶችን ገንበታለች እንዲሁም የተፈጥሮ ወንዞቿን በወንዝ ዳርቻ ልማት በማልማት ልዩ ገኝታ እንዲላበሱ ከተማዋ ለነዋሪዎች እና ለቱሪስቶች ምቹ እንድትሆን የማድረግ ስራዎችን በመስራት ትገኛለች ።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review