AMN – መጋቢት 1 /2018 ዓ.ም
የአእምሮ ጤና ችግር በማንኛውም የዕድሜ ክልል እና የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሊያጋጥም የሚችል የጤና እክል ነው።
በዓለም ጤና ድርጅት መረጃ መሠረት፣ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ የአእምሮ ጤና እክሎች ይጠቃሉ።
የአእምሮ ጤና መታወክ በአንድ ምክንያት ብቻ የሚከሰት ሳይሆን፣ በተለያዩ ውስብስብ ሁኔታዎች ጥምረት የሚመጣ መሆኑን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የአእምሮ ህክምና ክፍል ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ቤተልሄም ኢርከኖ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ከውስብስብ ሁኔታዎች ጥምረት በጭንቅላት ውስጥ ያሉ የኬሚካሎች መዛባትን፣ የዘር ውርስን እና በአንጎል ላይ የሚደርሱ አካላዊ ጉዳቶችን ያጠቃልላል ብለዋል።

በልጅነት ጊዜ የሚደርስ ከፍተኛ ጥቃት፣ ከባድ የሐዘን ስሜት እና ከሌሎች ሰዎች ጋር የመግባባት ችግርን የመሳሰሉ ሥነ-ልቦናዊ ተፅዕኖዎች ለችግሩ መባባስ ዋነኛ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
ከግለሰባዊ ሁኔታዎች ባለፈ እንደ ከባድ የኑሮ ጫና፣ ሥራ አጥነት፣ መድልዎ እና ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ብቸኝነት ያሉ ማህበራዊና አካባቢያዊ ሁኔታዎች ለሕመሙ መከሰት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ዶ/ር ቤተልሄም አብራርተዋል።
እንደ ዶ/ር ቤተልሄም ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ውጤታማ ሕክምና አግኝተው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ የሚችሉባቸው ሰፊ አማራጮች አሉ።
የመጀመሪያው የሥነ-ልቦና ምክር እና ሕክምና ሲሆን፣ ግለሰቦች ስለ ስሜታቸው፣ ስለ ሃሳባቸው እና ስለ ባሕሪያቸው ከባለሙያ ጋር እንዲወያዩ በማድረግ ለውጥ እንዲያመጡ ይደረጋልም ብለዋል።
በተለይም የባሕርይ ለውጥ ሕክምና፤ ግለሰቦች አሉታዊ አስተሳሰቦችን እንዲለዩ እና ጤናማ በሆኑ መንገዶች እንዲተኩ በማገዝ ረገድ ውጤታማነቱ የተረጋገጠ ዘዴ መሆኑን አብራርተዋል።

ከምክር አገልግሎቱ ጎን ለጎን የአንጎል ኬሚካሎችን ሚዛን ለመጠበቅ የሚረዱ መድኃኒቶች በሐኪም ትዕዛዝ የሚሰጡ ሲሆን፣ እነዚህም የጭንቀት፣ የድብርት እና የከባድ የአእምሮ መታወክ ምልክቶችን ለመቀነስ ይረዳሉ ብለዋል።
ዛሬ ላይ ዘመናዊው ሕክምና ከንግግር እና ከመድኃኒት ባለፈ ቴክኖሎጂን መጠቀም የጀመረ መሆኑን ዶ/ር ቤተልሄም ገለጸው፣ እንደ መግነጢሳዊ ሞገዶችን በመጠቀም የአንጎል የነርቭ ሴሎችን ማነቃቃት እና በዲጂታል ቴራፒ አማካኝነት የሚሰጡ የቪዲዮ ኮንፈረንስ የምክር አገልግሎቶች የሕክምናውን ተደራሽነት እያሰፉት ይገኛሉ ብለዋል።
ማንኛውም የሕክምና ሂደት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው የተቀናጀ ማህበራዊ ድጋፍ ሲታከልበት መሆኑን ዶ/ር ቤተልሄም አብራርተው፤ ጎን ለጎን ቤተሰብን ያሳተፈ ድጋፍ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የተመጣጠነ ምግብ እና በቂ እንቅልፍ ማግኘት ከችግሩ ፈጥኖ ለማገገም ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።
የአእምሮ ሕመም እንደ ማንኛውም አካላዊ ሕመም ሊታከም የሚችል መሆኑን በመገንዘብ፣ ማህበረሰቡ ለሕመሙ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት በመቀነስ ሕመምተኞች ሳይዘገዩ ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ ማበረታታት ይገባል ብለዋል።
በበረከት ጌታቸው