AMN – 30 / 2018ዓ.ም
የነዋሪው የቅሬታ መንስኤ ሆነው የቆዩትን የአየር ጤና፣ ወለቴ እና የአውቶብስ ተራ መሳለሚያ መንገዶች ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ የመንገዶቹን የግንባታ የሥራ ሂደት በመስክ ምልከታ ገምግመዋል።
አካባቢው ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለበት መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች ፣ መንገዱን ማስፋት ስላስፈለገ ፣ ዲዛይን በተደረገው ልክ የአካባቢ የወሰን ማስከበር ችግሮች አጋጥሞ የነበረ በመሆኑ እና የመጀመሪያውን ኮንትራክተር መቀየር በማስፈለጉ ሂደቱ በተወሰነ ደረጃ መዘግየቱን ከንቲባዋ አስረድተዋል፡፡
ለሁለተኛ ኮንትራት ከተሰጠ በኋላ ግን የዘገየውን ጊዜ ለማካካስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተሰራ ያለ መንገድ መሆኑን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል፡፡
የአውቶቡስ ተራ – መሳለሚያ – 18 ማዞሪያ አዲስ የአስፓልት መንገድ ወደ 3.3 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ፣ ትልቅ የመሸጋገሪያ ድልድይ እና የታች መተላለፊያን ያካተተ ነው፡፡

ለመንገድ ግንባታ የተቀመጠውን የግንባታ ደረጃ በተሟላ ሁኔታ እንተገብራለን ያሉት ከንቲባዋ ይህ መንገድ በሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ ለመጨረስ ተግተን ሌትና ቀን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሌላኛው የጎበኙት የአየር ጤና – ካራ ወለቴ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን፣ 5.6 ኪሎ ሜትር ይረዝማል፡፡
መንገዱ አዲስ አበባን ወደ ጅማ እና ሆሳዕና ከሚወጣው መንገድ ጋር የሚያስተሳስር ቀልጣፋ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ነው፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ የነበረበት ችግር ተቀርፏል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሥራው በፍጥነት ወደ ማጠናቀቅ ደረጃ መድረሱንና በሚቀጥሉት ሁለት ወራቶች በማጠናቀቅ ሕዝቡን እንክሳለን ብለዋል፡፡
በዚህ ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ 140 የሚደርሱ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 104 የሚሆኑት በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በራስ አቅም እየተገነቡ ይገኛሉ።
ቀድሞ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲሰራ የተለያዩ የወሰን ማስከበር ክርክሮች ራሱ በመብራትም ፣ በህዝብም መ፣ንገዱ ላይ በሚሰሩ አካላትም ይነሳ እንነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ ፣ አሁን ያ ታሪክ አዲስ አበባ ማብቃቱን ገልጸዋል፡፡
ልማት ይዘን በመቅረባችን ሕበረተሰቡ እንዲሰራ የሚተባበር፣ በርቱ የሚል፣ ቡና እያጠጣ እያበረታታ አብሮ የሚሰራ ሆኗል ብለዋል፡፡
በታደሰ ሽፈራዉ