ውበትን ለተፈጥሮ ጥበቃ የገበረችው መሐንዲስ

You are currently viewing ውበትን ለተፈጥሮ ጥበቃ የገበረችው መሐንዲስ

AMN- መጋቢት 1/2018 ዓ.ም

ሴትነት ወደ ዕድል የሚቀየር ኃይል ነው የምትለው ደሊና ገብረማሪያም፣ በዓለም 10 ምርጥ ተወዳዳሪዎች ውስጥ በመካተት አፍሪካን የመራች ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴት ናት።

ከእናቷ የወረሰችውን የተፈጥሮ ፍቅር ከኢንጂነሪንግ ትምህርት ካገኘችው እውቀቷ ጋር በማቀናጀት፣ ስለ አካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ የመፍጠር ስራን የሕይወቷ ዋነኛ ግብ አድርጋ ተነስታለች።

የ2017 የኢትዮጵያ ሚስ ኧርዝ አሸናፊዋ ደሊና ገብረማሪያም፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያን ወክላ በመቅረብ ከአፍሪካ 1ኛ እንዲሁም ከዓለም 10 ምርጥ ተወዳዳሪዎች ውስጥ መካተት የቻለች ስኬታማ ሞዴል ናት።

ደሊና ከሞዴሊንግ ባሻገር በሲቪል ኢንጂነሪንግ እና በአካባቢ ጤና ዘርፍ ያላትን እውቀት በመጠቀም ለአረንጓዴ አሻራ እና ለአካባቢ ጥበቃ በቁርጠኝነት እየሰራች ትገኛለች። ስለ ስኬት ጉዞዋ፣ ስለ አካባቢ ጥበቃ ፍቅሯና ስለ ሴትነት ያላትን እይታ ከ ኤ ኤም ኤን ጋር በነበራ ቆይታ አብራርታለች፡፡

የደሊና የሞዴሊንግ ፍላጎት የጀመረው ገና በልጅነቷ ነበር። በቴሌቪዥን የምታያቸው ሞዴሎች ይስቧትና “እኔም እንደነሱ ብሆን” የሚል ህልም ነበራት። ይህ የልጅነት ፍላጎቷ ውድድሮች ላይ እስከ መሳተፍና አሸናፊ እስከ መሆን አድርሷታል።

በሞዴሊንግ ዘርፍ በርካታ የውድድር አይነቶች ቢኖሩም ደሊና “ሚስ ኧርዝን” የመረጠችበት የራሱ የሆነ ምክንያት አላት። ውድድሩ በዋናነት የሚያተኩረው በአካባቢ ጤና፣ በአረንጓዴ አሻራ እና ዓለም አቀፍ የሙቀት መጨመርን በመቀነስ ላይ ነው።

የሚስ ኧርዝ ዓላማ ከእኔ ማንነት ጋር ስለሚጣጣም ነው የመረጥኩት፤ እጽዋትን መትከል፣ አካባቢን ማጽዳት እና ለቀጣዩ ትውልድ ንጹህ አየርና ተፈጥሮን ማቆየት ግዴታችን ነው ብዬ አምናለሁ ትላለች።

ይህ ለተፈጥሮ ያላት ጥልቅ ፍቅር የመነጨው ከቤተሰብ አስተዳደጓ እንደሆነ የምትናገረው ደሊና፣ ነርስ የሆኑት እናቷ ለታካሚዎች ከመድኃኒት በላይ ንጹህ አየርና አረንጓዴ ተፈጥሮ ያስፈልጋቸዋል ብለው ያምኑ ስለነበር፣ ደሊናም ይህንኑ እውነት ይዛ አድጋለች።

በኢትዮጵያ አሸናፊ ከሆነች በኋላ ቀጣይ ጉዞዋ በቢውቲ ፔጀንት ወደታወቀችው ፊሊፒንስ ነበር። እዚያም በነበራት ቆይታ ደሊና ተብላ ሳይሆን “ሚስ ኢትዮጵያ” ተብላ በመጠራቷ ትልቅ ኩራት ይሰማት እንደነበር ትገልጻለች። በውድድሩም ከ17 የአፍሪካ ሀገራት ተወዳዳሪዎች ጋር በመወዳደር የአፍሪካ ቁንጮ መሆን ችላለች።

በተለይም በውድድሩ የብስለት መለኪያ ዙር ላይ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 350 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል የዓለም ሪከርድ መስበሯን ለዓለም በማስተዋወቅ አርአያነታችንን መስክራለች።

ደሊና በአሁኑ ወቅት በዋናነት ትኩረቷን ያደረገችው ስለ አካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ሲሆን፣ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ስለ አካባቢ ጥበቃ ትምህርት ከመስጠት ባለፈ፣ በሙያ ዘርፏ አዳዲስ ግንባታዎች ሲከናወኑ ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተስማሚ እንዲሆኑ ፕሮጀክቶችን ቀርፃ እየሰራች ትገኛለች።

ስለ ሴትነት ስትገልጽም ሴት መሆን እንደ አጠቃቀማችን ነው፤ ጎበዝ በመሆን እና በራስ በመተማመን ሴትነትን ወደ ዕድል በመቀየር ፍሬያማ መሆን ይቻላል ብላለች፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review