AMN – መጋቢት 2/2018 ዓ.ም.
ከዓለማችን ጠቅላላ ሕዝብ መካከል ከሶስት በመቶ የማያንሰው የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት እንዳለበት የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህንን ቁጥራዊ መረጃ ወደ ኢትዮጵያ ስንመነዝረው ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የአዕምሮ እድገት ውስንነት ተጠቂ መሆናቸው ይነገራል፡፡
እነዚህ ዜጎች የገጠማቸው ሕመም ከሃይማኖትና ቁጣ ጋር በማያያዝ አብዛኞቹ ከፍተኛ መገለል እንደሚደርስባቸው የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የተቋቋሙ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ይገልጻሉ፡፡
በርካታ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ተጠቂዎች ማኅበረሰቡ ባለው የተሳሳተ ግንዛቤ ምክንያት በቤት ውስጥ ተሸሽገው፣ ከዕኩዮቻቸው ጋር እንዳይጫወቱ ተደርገው፣ በእግሮቻቸው ላይ ሰንሰለት ታስሮቦቸው የሰቆቃ ሕይወት ይኖራሉ የምትለው ተጠቂ ወንድም ያላት ምኅረት ንጉሴ ናት፡፡
ይህንን ችግር ይቀርፋል የተባለው ‹‹ስፔሻል ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ›› ከተመሠረተ ሰባት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎችን በስፖርት ማሳተፍን መዳረሻ አድርጎ የተቋቋመው ስፔሻል ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ የተወሰነ ስኬት አስመዝግቤያለሁ ይላል፡፡
በግብጽ ካይሮ፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዱባይ እንዲሁም በጀርመን በርሊን በተካሄዱ አሕጉር ዓቀፍና ዓለም ዓቀፍ የስፔሻል ኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን አመርቂ ውጤት ይዘው መመለሳቸውን የስፔሻል ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ናሽናል ዳይሬክተር ትርሲተወልድ አበባየሁ ታስታውሳለች፡፡

በዚህ መነሻነት በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአስር ሺህ በላይ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ዜጎችን አትሌቲክስን ጨምሮ በተለያዩ ስፖርቶች የማሳተፍ ዕቅድ ተነድፎ ወደ ትግበራ መገባቱን ትርሲተወልድ ትናገራለች፡፡
የዓለም ስፔሻል ኦሊምፒክ ውድድር በመጪው ዓመት መባቻ በቺሊ ሳንቲያጎ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ እስከ 25 ተወዳዳሪዎችን እንድታሳትፍ ፍቃድ አግኝታለች፡፡ በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመምረጥ ከመጋቢት 4 እስከ 6 2018 በአዲስ አበባ ሀገር አቀፍ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሔዳል፡፡
በውድድሩ ላይ አምስት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሳተፉ የስፔሻል ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ኢንጂነር ግርማ ዘውዱ ይናገራሉ፡፡
‹‹ውድድሩ በቤት ውስጥ ተደብቀው የሚኖሩ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ተጠቂዎችን ወደ አደባባይ የሚያወጣ፤ እኛም ዕድል ቢሰጠን ለሀገሪቱ የበኩላችንን ሚና እንደምናበርክት የምናሳይበት ነው›› ያሉት ደግሞ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ናቸው፡፡
ውድድሩን በስኬት ለማካሄድ የሰለጠኑ ዳኞች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ አሰልጣኞችና የውድድር ባለሙያዎች መዘጋጀታቸውን የገለጸችው ደግሞ የስፔሻል ኦሊምፒክ አትሌቶች አሰልጣኟ ሸዋጌጥ ክብረት ናት፡፡
የመጀመሪያው ሀገር ዓቀፍ ውድድር አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንደሚካሄድ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከስፔሻል ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
በታምራት አበራ